ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን በኃይል እና በወረራ ማሳካት አትፈልግም፡ ጠ/ሚ ዐቢይ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገራቸው በኃይል እና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው ነገር እንደሌለ በመግለጽ በአጎራባች አገራት ላይ ወረራ የመፈጸም ፍላጎት እንደሌላት ተናገሩ።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንደሚያስፈልጋት ለአገሪቱ ምክር ቤት አባላት ያደረጉት ንግግር በአካባቢው ውጥረትን እና ግጭትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋትን ፈጥሮ ቆይቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ116ኛው የኢትዮጵያ ሠራዊት ቀን ዛሬ ጥቅምት 15/2016 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ወታደራዊ ትርኢቶች በተከበረበት ጊዜ ነው ኢትዮጵያ በኃይል እና በወረራ ፍላጎቷን ማሳካት እንደማትሻ የተናገሩት።
የአገሪቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውይይት ያስፈልጋታል ስትል ወራራ ሊካሄድ ይችላል የሚል ስጋት ይደመጣል” በማለት አገራቸው የውይይት እንጂ የግጭት ፍላጎት እንደሌላት በሥነ ሥርኣቱ ላይ ተናግረዋል።
ጨምረውም “ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ለአገር መከላከያ ሠራዊት ማረጋገጥ የሚፈልገው፣ ኢትዮጵያ በኃይል እና በወረራ ማሳካት የምትፈልገው አንዳች ነገር የለም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ለጋራ ጥቅም፣ ለጋራ ዕድገት፣ ለጋራ ብልፅግና፣ ሁሉም አሸናፊ በሚሆንበት መንገድ የጋራ ጥቅማችንን ለማስከበር እንደምትሠራ በመግለጽ፣ “በወንድሞቻችን ላይ ቃታ የማንስብ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ብለዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሲነሳ የነበረው የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እና በብሔራዊ ቴሌቪዥን በተላለፈ ስብሰባ የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ጉዳይ ውይይት የሚያስፈልገው የሕልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ ግን የባሕር በር የሌላት አገር የሆነችው ከ30 ዓመት በፊት ኤርትራ ነጻ መውጣቷን ተከትሎ ነው።
ከዚያ በኋላ አገሪቱ ለገቢ እና ለወጪ ንግዷ የትንሿን ጎረቤት አገር ጂቡቲን ወደብ በመጠቀም ላይ ትገኛለች።
“ቀይ ባሕር እና አባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ፣ ከኢትዮጵያ የተቆራኙ ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ጥፋት መሠረት ናቸው” በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ መሸሽ እንደማያስፈልግ ተናግረው ነበር።
ከቅርብ ወራት በፊት ለኢትዮጵያ የባሕር በር ስለማስገኘት በይፋ ሲባል ባይሰማም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ አገሪቱ የፈረሰውን የባሕር ኃይሏን መልሳ ማቋቋሟ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላነሱት የባሕር በር ጥያቄ ኤርትራ፣ ጂቡቲ እና ሶማሌላንድ አማራጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ በመዘርዘር፣ ይህ የኢትዮጵያ ፍላጎት ሊሳካባቸው የሚችሉባቸው ያሏቸውን ከግጭት ውጪ ያሉ አማራጮችን አስረድተዋል።
ባለፉት ሳምንታት ዋነና መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርን ተከትሎ ኤርትራ፣ ጂቡቲ እና ሶማሊያ በወደብ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ በኩል ስለተነሳውን ሃሳብ እንደማያውቁ መግለጻቸው ይታወቃል።
ይህ ለኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ ከረጅም ጊዜ ጠላትንት በኋላ ከኤርትራ ጋር የተሻሻለውን ግንኙነት ሊያበላሸው እንደሚችል እንዲሁም ከጂቡቲ እና ከሶማሊያ ጋርም ውጥረትን ያስከትል ይሆንል የሚል ስጋት ፈጥሮ ነበር።