የአዲስ ዓመት ሎተሪ የ16 ሚሊዮን ብር አሸናፊ እየተፈለገ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ2016 ዓ. ም. አዲስ ዓመት ሎተሪ የ16 ሚሊዮን ብር አሸናፊ እስካሁን አለመገኘቱን የብሔራዊ ሎቶሪ አስተዳድር ገለጸ።
አሸናፊ የሚያደርገውን ትኬት የያዘው ሰው በኦሮሚያ ክልል፣ ቱሉ ቦሎ ከተማ ወይም ዙሪያ ሊሆን እንደሚችል የአስተዳደሩ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከትልልቆቹ ሎተሪዎች እንዱ የሆነው የእንቁጣጣሽ ሎቶሪ አዲስ ዓመት ዋዜማ ላይ ወጥቶ እንደነበርና 4 ሚሊዮን ብር የሚያስገኘው ትኬት ገዝቶ የነበረ የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ ግለሰብ ከሰሞኑ ሽልማቱን እንደወሰደ ገልጸዋል።
ግለሰቡ ለሥራ ቱሉ ቦሎ በሄደበት ትኬቱን ሐምሌ 2015 ዓ.ም. ላይ ገዝቶ እንደነበር አክለዋል።
ዕጣው የ20 ሚሊዮን ብር ሲሆን የአዲስ አበባው ግለሰብ 4 ሚሊዮን ብሩን ከወሰደ በኋላ የቀረው 16 ሚሊዮን ብር እጣ የደረሰው ግለሰብ ነው እስካሁን ያልተገኘው።
“16 ሚሊየኑ ብር ግን እስካሁን አልመጣም” ብለዋል አቶ ቴዎድሮስ።
"ዕድለኛው ትኬቱን ቱሉ ቦሎ ውስጥ እንደገዛው ነግሮናል። ስለዚህ የተቀረውን ትኬት የያዘው ቱሉ ቡሎ ውስጥ ነው የሚሆነው። እየጠበቅነው ነው” ብለዋል።
20 ሚሊዮን ብር የሚያሸልመው ቁጥር 1820259 መሆኑ ተገልጿል።
የብሔራዊ ሎተሪ ዕጣ ከወጣ በኋላ በየትኛው ቅርንጫፍ ከስንት ቁጥር እስከ ስንት ያሉት ትኬቶች እንደተሰራጩ ስለሚታወቅ ትኬቱ የተሸጠበትን አካባቢ ማወቅ እንደሚቻል አስረድተዋል።
የቱሉ ቦሎ ነዋሪዎች ወይም ለገበያ ከገጠር ከተማ የመጡ ሰዎች ትኬቱን ገዝተው ሊሆን እንደሚችል የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ አሸናፊ የሚያደርገውን ትኬት የገዛ ሰው ገንዘቡን እስከሚወስድ የሚጠበቀው ለስድስት ወራት እንደሆነ ተናግረዋል።
“እስከ የካቲት 30 ድረስ ዕድለኛውን እንጠብቃለን” ብለዋል።
እስከ የካቲት 30፣ 2016 ዓ. ም. ድረስ ዕድለኛው ብሩን ካልወሰደ ገንዘቡ ወደ መሥሪያ ቤቱ ገቢ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ይህ የእንቁጣጣሽ ሎቶሪ ከ2 ሚሊዮን በላይ ትኬት እንደተሸጠና የድርጅቱም ዓመታዊ ሽያጭ 2 ቢሊዮን እንደደረሰ ገልጸዋል።
ከአራት ዓመት በፊት ሽያጭ አንድ ቢሊዮን ብር ነበር።
በ1954 ዓ. ም. አንደኛ እጣ 5 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን አሁን 20 ሚሊዮን ብር ደርሷል።
ከአሥር ዓመታት በፊት በአመት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ትኬት አይሸጥም ነበር። አሁን ግን እስከ 200 ሚሊዮን ብር ሊደርስ ይችላል።
የሰዎችና የአገር ገቢም ማደግ እንዲሁም የመሠረተ ልማት ልማት መስፋፋት የትኬት ሽያጭን እንደጨመረው ገልጸዋል።
አስገራሚ የሎቶሪ ገጠመኞች
ከዚህ ቀደም በ1986 ዓ. ም. ብሩ የሚሰጥበት ቀነ ገደብ ሊጠናቀቅ ግማሽ ቀን ሲቀረው ገንዘቡን የወሰደ ሰው እንደነበር አስታውሰዋል።
ከመቀለ የመጡ ነጋዴ ትኬታቸውን በመጨረሻው ሰዓት ዐይተው አሸናፊ እንደሆኑ አውቀው ነበር።
የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ደግሞ የ20 ሚሊዮን ብር እጣ ከሦስት ትኬቶች አንዱ የነበው ግለሰብ ቀነ ገደቡ ሊጠናቀቅ አምስት ቀን ሲቀረው ወደ ድርጅቱ እንደሄደ ገልጸዋል።
ወራት ሲቀራቸው የሚሄዱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ እስከነጭራሹ ገንዘባቸውን ሳይወስዱ እንደሚቀሩ ተናግረዋል።
“በጣም በርካቶች በፍላጎት ትኬቱን ይገዙና ቁጥሩን ለማየት ግን ፍላጎት አይኖራቸውም” ብለዋል አቶ ቴዎድሮስ።
አንዳንዶች እጣው ከመውጣቱ አስቀድመው ትኬቱ እንደተሰረቀባቸው ገልጸው ቁጥሩን ግን ለድርጅቱ የሚነግሩ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ፍርድ ቤት ሄደው ትኬታቸው እንደተሰረቀና አሸናፊው ቁጥር የነሱ እንደሆነ በማጻፍ የፍርድ ቤት ዕግድ ይዘው ወደ ድርጅቱ እንደሚሄዱም አስረድተዋል።
አንድ ከባለቤታቸው ጋር የተለያዩ ግለሰብ አንድ ሚሊዮን ብር እጣ የደረሰው ትኬት ባለቤታቸው ጋር እንዳለ እሳቸው ግን ቁጥሩን እንደሚያውቁት ገልጸው አንድ ሚሊዮኑን ለመውሰድ የሄዱበትን አጋጣሚም አስታውሰዋል።












