ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሳዑዲ አረቢያ በተደረገው የአሜሪካ እና ሩሲያ የሰላም ንግግር ልዑካኑ እነ ማን ናቸው?
ማክሰኞ፣ የካቲት 11/ 2017 ዓ.ም አሜሪካ እና ሩሲ በሳዑዲ አረቢያ ያካሄዱት የሰላም ንግግር የሞስኮን ከምዕራቡ ዓለም መገለል የቋጨ ነው።
የሁለቱ ተደራዳሪ ቡድን ሦስት አሜሪካዊያንን እና ሦስት ሩሲያዊያንን አካቷል።
የንግግሩ ተሳታፊዎች መድረኩ "ለከፍተኛ ንግግር" መደላደል የሚፈጥር መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ሁለቱ አጋራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ ተስማምተዋል።
የዚህ ንግግር ተሳታፊዎች እነ ማን ናቸው? ሁለቱ ኃያላን አገራትን ለማቀራረብ ምን ፋይዳ ይጫወታሉ?
የሳዑዲው ንግግር ከመካሄዱ ሦስት ቀናት አስቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በስልክ መክረዋል።
ማክሰኞ ዕለት ከተደረገው ንግግር በኋላ ሚኒስትሩ ጦርነቱን ለማቆም እና የአገራቱ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል ሩሲያ ዝግጁ መሆኗን አምኛለሁ ብለዋል።
ሩቢዮ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆም ለረጅም ጊዜ ሲወተውቱ ቆይተዋል። በአውሮፓውያኑ 2024 አሜሪካ ልታቀርብ የነበረውን የስድስት ቢሊዮን ዶላር የመከላከያ እርዳታ ማዕቀፍ ተቃውመው ድምፅ ሰጥተዋል።
"አንድ ስብሰባ [ለጦርነቱ] መፍትሄ አይሰጥም" ሲሉ ከወዲህ ማስጠንቀቂያ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ዩክሬን እና አውሮፓ መሳተፍ አለባቸው ብለዋል።
"ማንም እያገለልን አይደለም" በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።
የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ማይክ ዋልትዝ ከስብሰባው በኋላ ንግሮች ለጦርነቱ በጊዜያዊ ሳይሆን በዘላቂ ለማስቆም የሚገፉ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ነገር ግን አማካሪው አሜሪካ ለዩክሬን ላደረገችው በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ክፍያ እንደምትሻም ጠቁመዋል።
ከዚህ ባሻገርም ዩክሬን የማዕድን ሀብቷን ከአሜሪካ ጋር በአጋርነት ልታጋራ እንደሚገባም እምነታቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ንግግር አዲስ ፊት ሆነው ብቅ ያሉት ስቲቭ ዊትኮፍ ሲሆኑ ባለፈው ሳምንት በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቭላድሚር ፑቲን ጋር እንዲነጋገሩ የተሾሙ ናቸው። ስቲቭ ዊትኮፍ የዋይት ሃውስ የመካከለኛው ምስራቅ መልዕክተኛ ናቸው።
ሩሲያ ለሳዑዲው ንግግር ሁለት ከፍተኛ ዲፕሎማቶችን መርጣለች።
ሁለቱም ዲፕሎማቶች ረጅም ዓመታት ያገለገሉ እና በአሜሪካዊያንም በደንብ የሚታወቁ ናቸው።
የፑቲን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ዩሪ ዩሽኮቭ እና እ.አ.አ ከ2004 ጀምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሰርጌ ላቭሮቭ በሩሲያ የተላኩ ናቸው።
ዲፕሎማቶቹ ሦስት ዓመታት በደፈነው የዩክሬን ጦርነት የፑቲንን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በመምራት የሚታወቁ ሲሆኑ፤ ሰርጌ ላቭሮቭ የሞስኮን መልዕክቶች በማስተላለፍ ተጠምደው ከርመዋል።
በማክሰኞው ስብሰባም ላቭሮቭ ይህን ኃላፊነታቸውን የተወጡ ሲሆን፤ ከአሜሪካ ልዑካን ሞስኮ የኃይል ዘርፉ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ገታ እንድታደርግ ለቀረበላቸው ምክረ ሀሳብ ሩሲያ በዩክሬን የየሕዝብ መገልገያ ላይ አነጣጥራ አታውቅም ብለዋል።
ይህም ሩሲያ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ጣቢያዎችንን በማጥቃት የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ በዩክሬን መደበኛ ሕይወት እንዲሆን ለማድረጓ የተሰጠ ማስተባበያ ነው።
የቀድሞው በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር የነበሩት ዩሪ ዩሽኮቭ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ በተመለሱ በቀናት ውስጥ አሜሪካ "ተጨባጭ ምልክት" ከላከች ለንግግር ዝግጁ ነን ብለው ነበር።
ሦስተኛው የሩሲያ ልዑክ ኪሪል ዲሚትሪቭ ፑቲን በሳዑዲው ንግግር የምጣኔ ሀብትን ጠቀሜታ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳዩበት ነው።
የሩሲያ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈንድ ኃላፊ ሲሆኑ፤ የምጣኔ ሀብት ግንኙነትን በተመለከተ ለመነጋገር ባልደረቦቻቸውን ዘግየት ብለው ነበር የተቀላቀሏቸው።
በእስረኞች ልውውጥ ከአሜሪካው ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር ቁልፍ ሚና የተጫወቱም ናቸው።
የሀርቫርድ ንግድ ትምሕርት ቤት ምርቁ እና በአሜሪካ ግዙፍ የገንዘብ ተቋማት የሰሩ ሲሆኑ የአሜሪካን የፋይናንስ እና የንግድ ዘርፍ በደንብ ዘርፍ በደንብ ከሚያውቁ ጥቂት ሩሲያዊያን መሀል እንደሆኑም ይነገራል።
የሁለቱ አገራትን ንግግር ሁለት የሳዑዲ ባለስልጣናት ቢያስጀምሩትም ንግግሩ ላይ ግን አልተሳተፉም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፈይሰል ቢን ፈርሃን በዚህ ዓመት የሳዑዲ ከፍተኛ ዲፕሎማት በመሆን ንቁ ሚና ተጫውተዋል።
የሳዑዲ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሙሳድ አል አቢንም አገራቸው ከሶሪያ አዲስ መሪ ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር ቁልፍ ሰው ናቸው።