ቡርኪናፋሶ ጦሯ በጅምላ ግድያ መወንጀሉን አስመልክቶ ባቀረበው ዘገባ ቢቢሲን አገደች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ቡርኪናፋሶ የጦር ሰራዊቷ በጅምላ ግድያ መወንጀሉን አስመልክቶ ባቀረቡት ዘገባ ቢቢሲ እና የአሜሪካ ድምጽን አገደች።
የሁለቱም ጣቢያዎች ስርጭቶች መቋረጣቸውን እንዲሁም የድርጅቶቻቸው ድረገጾች ለሁለት ሳምንታት መታገዳቸውን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
ሁለቱ ሚዲያዎች መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው ሂውማን ራይትስ ዋች ያወጣውን ጦሩ ንጹሃን ዜጎችን መግደሉን ዋቢ በማድረግ ነው በዘገቦቻቸው የሸፈኑት።
ሂውማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ የቡርኪናፋሶ ጦር በየካቲት ወር ቢያንስ 223 ንጹሐን ዜጎችን ጨፍጭፏል ብሏል።
ጦሩ ከሁለት ዓመት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ ምዕራብ አፍሪካዊቷን አገር እየመራ ይገኛል።
ሂውማን ራይትስ ዋች ባቀረበበት ጭፍጨፋ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም። የሰራዊቱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ቢቢሲ ላቀረበላቸው ጥያቄም መግለጫ ካወጡ በዚያ እንደሚመልሱት ተናግረዋል።
የቡርኪናፋሶ የሚዲያ ተቆጣጣሪ ሐሙስ ዕለት በሰጠው መግለጫ ሁሉም ሚዲያዎች የመብት ድርጅቱ ያወጣውን ሪፖርት እንዳይዘግቡ አስጠንቅቆ፣ ይህንን ትዕዛዝ በማያከብሩ ላይ ማዕቀብ እንደሚጣል የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
“እገዳው ቢቢሲ ታዳሚዎችን ገለልተኛ እና ትክክለኛ ዜና ለማድረስ ለሚያደርገው ጥረት ችግር ይፈጥራል። የቀጠናውን ማህበረሰብ ባማከለ መልኩ ለህዝብ ጥቅም ያለ ፍርሃት መዘገባችንን እንቀጥላለን” ሲሉ የቢቢሲ ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።
የአሜሪካ ድምጽ በበኩሉ አርብ ዕለት ባወጣው ጽሑፍ ስለ ቡርኪናፋሶ ያወጣው ዘገባ ትክክለኛነት ጠቅሶ “በአገሪቱ ውስጥ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንሸፍናለን” ብሏል።
ሂውማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት መሰረት የቡርኪናፋሶ ጦር ሰሮ በተባለችው ግዛት 179 ሰላማዊ ሰዎችን ሲገድል እንዲሁም በአቅራቢያዋ በምትገኘው ኖንዲን ደግሞ 44 ንጹሃን ዜጎችን ገድሏል ብሏል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የታጠቁ እስላማዊ ተዋጊዎችን ይረዳሉ በሚል ውንጀላ ጦሩ በግዛቲቷ ነዋሪዎች ላይ የፈጸሙት የበቀል እርምጃ እንደሆነም ይታመናል።
የሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት የጅምላ ግድያውን በአገሪቱ በአስር አመታት ውስጥ የተፈጸመ “እጅግ የከፋ የሰራዊት ጥሰት” ነው ሲል ገልጾታል ።
ሚዲያዎቹ ጦሩ ፈጽሟቸዋል የሚባሉ ጥሰቶችን በሚዘግቡበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ሪፖርቶች የሰራዊቱን ሞራል ለመናድ ያለመ ነው የሚሉ ትችቶች ከወታደራዊው ጁንታ ደጋፊዎች ይሰማል።
ባለፈው ዓመታት ጦሩ የፈረንሳዩን ሚዲያ ለ ሞንድ፣ ዘ ጁየን አፍሪክ መጽሔት እንዲሁም የፈረንሳይ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ላ ቻይን ኢንፎ እና ፍራንስ 24ን አግዶ ነበር።












