ደሞዝ በጊዜው የማይከፈላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ጭንቀት በወላይታ

የፎቶው ባለመብት, wolita Comm.
በአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ዞን የደሞዝ መዘግየት እና ተቆራርጦ መከፈል ችግር ውስጥ እንደከተታቸው የመንግሥት ሠራተኞች ተናገሩ።
ወላይታ ዞን 16 ወረዳዎች እና ስድስት የከተማ አስተዳደሮችን የያዘ አስተዳደር ሲሆን፣ 64 ሺህ ሚሆኑ የመንግሥት ሠራተኞችም አሉት።
ዞኑ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሠራተኞች የደሞዝ ክፍያ ላይ ቅሬታዎች ሲነሱበት የቆየ ቢሆንም፣ ችግሩ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ተባብሶ መቀጠሉን ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ደሞዝ በወቅቱ አለመከፈል እና ክፍያ ሲፈጸም ደግሞ በፈረቃ አሊያም ተከፋፍሎ እንደሚፈጸም፣ ይህም በኑሯቸው ላይ ጫና ከማሳረፍ ባለፈ በአካባቢው ላይ ቀውስ እያስከተለ ነው ብለዋል።
በዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሠራተኛ የሆኑ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ ግለሰብ በወላይታ ዞን ያለው የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ አከፋፈል ሁኔታ አብዛኛውን ሠራተኛ ጭንቀት ውስጥ ከትቶታል ይላሉ።
የመጋቢት ወር ደሞዝ ሚያዚያ 17/2016 ዓ.ም. እንደተከፈላቸው የሚናገሩት ሠራተኛው፤ ይህም ሙሉ ደሞዛቸው ሳይሆን “60 እና 70 በመቶው” የሚሆነው ብቻ ተቆርጦ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
ሠራተኞች የሚዘገይ ደሞዝ እና በአሁኑ ወቅት ያለው የኑሮ ውድነት ቤተሰቦቻቸውን እና እራሳቸውን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚደረገው ትግል ጭንቀት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል።
በብድር መኖር
በዞኑ ዋና መቀመጫ ሶዶ ከተማ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑ ሌላ የመንግሥት ሠራተኛ፤ የደሞዝ አከፋፈሉን ሲያስረዱ፤ “ሁልጊዜ ደሞዝ ይቆራረጣል። 30 ካለፈ በኋላ [የወሩ መጨረሻ] እስከ 10 ባለው ነው የሚገባው። ሲከፈልም 40 በመቶ፣ 50 በመቶ፣ 60 በመቶ አድርገው ነው የሚያስገቡት። ቀሪው ቀጣይ ደሞዝ እስኪመጣ ድረስም አይገባም” ይላሉ።
በዚህም የመንግሥት ሠራተኛው ተስፋ እየቆረጠ ነው የሚሉት መምህሩ፤ “መኖር አቅቶናል” ሲሉ ጫናውን ይገልጻሉ።
“ልጆቻችንን ትምህርት ማስተማር አልቻልንም፤ መቀለብ አልቻልንም” የሚሉት መምህሩ፣ ወርሃዊ አስቤዛቸውን በዱቤ ለመግዛት እንደተገደዱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ተቀናንሶ የሚገባውን ደሞዝ እንደ ምንም ቆጥበን በብድር እቃ ከሱቅ እንወስዳለን። በደሞዝ ይከፈላል ተብሎ ነው አስቤዛ እና እህል የሚወሰደው። ከዚያ ደሞዝ ሲገባ የቀደመውን [ዕዳ] ከፍለን ቀጣዩን ደግሞ በብድር እንስወስዳለን” ሲሉ ጫናውን ያስረዳሉ።
የሥነ ልቦና ጉዳት እየደረሰብኝ ነው የሚሉ ሌላ የመንግሥት ሠራተኛ ደግሞ የቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻላቸው “ልጆቼ ጎዳና እንዳይወጡ ስል የቤት ኪራይ ተበድሬ ከፍያለሁ” ይላሉ።
የመጋቢት ወር ደሞዛቸው እስካሁን እንዳልተከፈላቸው የሚናገሩት በዞኑ በሚገኝ አንድ ጤና ጣቢያ ውስጥ የጤና ባለሙያ፤ “ሕይወታችን እየተናጋ ነው” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
“የተከራየሁት ቤት የዚህኛውን ወር ካልከፈልክ እያሉ ሞራሌን እየጎዱት ነው። ከየት አምጥቼ ነው የምከፍለው? እህል ካልተፈጨስ ምኑ ይበላል?. . . አስቤዛም የትኛውንም ነገር መግዛት አልተቻለም” ሲሉ ጫናውን የሚያስረዱት ባለሙያው፤ በባለቤታቸው ገቢ ምክንያት እንደ ባልደረቦቻቸው የከፋ ሁኔታ ውስጥ አለመውደቃቸውን ጠቅሰዋል።
የሕዝብ አገልግሎቶች መስተጓጎል
ለሕዝቡ የዕለት ከዕለት አግልግሎት የሚሠጡት የመንግሥት ሠራተኞች የሠሩበት ወርሃዊ ደሞዝ በአግባቡ ስለማይከፈላቸው በሥራቸው ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም አልደበቁም።
“የመንግሥት ሠራተኛው ሕዝብን እና መንግሥትን ማገልገል፤ ቢሮ መግባት አልቻለም። ልጆቹን ማስተማር፣ ሕይወቱን ማስቀጠል አልቻለም። እና ከባድ ችግር ውስጥ ነው ያለነው” በማለት ሌላ የመንግሥት ሠራተኛ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።
እንደ ትምህርት እና ጤና ባሉ ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሠራተኞች ሥራ በማቆማቸው ደጃቸውን እየዘጉ ነው ብለዋል።
በደሞዝ ምክንያት 24 ሰዓት መሥራት ያለባቸው የጤና ተቋማት ባለሞያዎች ምሽት እና በሳምንቱ ማብቂያ ቀናት ሥራ እንደማይገቡ የሚናገሩት የጤና ባለሙያ፤ ይህም ማኅበረሰቡ የህክምና አገልግሎት እንዳያገኝ እያደረገ ነው ይላሉ።
“ሞራሉ የተጎዳ የመንግሥት ሠራተኛ፤ የሚበላውን ያጣ የጤና ባለሙያ ታማሚውን ያክማል ተብሎ አይታሰብም። ላለመወቀስ ብለው ለመታየት አንድ ሁለት ሠዎች መደበኛውን የሥራ ሰዓት ስምንት ሰዓትን አክብረው የሚገቡ አሉ እንጂ ምሽት፣ ቅዳሜ እና እሁድ የጥበቃ ሠራተኛ እንኳን አይገኝም ሲሉ” ማኅበረሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ተጽዕኖ ይናገራሉ።
ቢቢሲ ያናገራቸው ሁለት መምህራንም ደሞዝ በሚዘገይባቸው ቀናት መምህራን ወደ ትምህርት ቤቶች እንደማይሄዱ እና ተማሪዎችም ከትምህርት ቤቶች እንደሚቀሩ ገልጸዋል።
“ሰው እየተራበ ማስተማር አይችልም። ደሞዝ ሳይከፍል ደግሞ ለምን አላስተማርክም ብሎ ማስገደድ አይቻልም። መምህራን በግል ትምህርት ቤቶች ካልሆነ በስተቀር ደሞዝ 30 አልፎ እስከ አምስት የማይገባ ከሆነ፤ መሠረታዊ ወጪያቸውን መሸፈን አይችሉም። ከዚህ ጋር ተያይዞ ትምህርት ቤቶች መምህራን ስለማይገቡ ዝግ ይሆናሉ” ሲሉ አንድ መምህር ተናግረዋል።
የገቢ እና ወጪ አለመመጣጠን
የወላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ በጀት ለአፈር ማዳበሪያ ዕዳ እና እንደ ውሎ አበል እንዲሁም ነዳጅን ለመሳሰሉ ወጪዎች ክፍያ እየዋለ ነው ሲሉ ቢቢሲ ያናጋራቸው ሠራተኞች ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።
ከአካባቢው መስተዳደር ምንም ምላሽ አላገኘንም በማለትም፤ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ ገብቶ ችግሩን እንዲፈታ ተማጽነዋል።
የወላይታ ዞን አስተዳደር የችግሩ ምንጭ “የገቢ እና የወጪ አለመጣጣም ነው” በማለት፤ የመጋቢት ወር ደሞዝ ከክልሉ በተገኘ ብድር ከሰሞኑ ስለመከፈሉ ተናግሯል።
የዞኑ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ መብራቱ ጳውሎስ “የጥሬ ገንዘብ እጥረት ነው” ሲሉ ለደሞዝ ቀውሱ ዋነኛ ምክንያትን ያስቀምጣሉ።
“አንድ ወረዳ ጡረታን ጨምሮ በወር 23 ሚሊዮን ብር ደሞዝ የሚከፍል አለ። ይሄ ወረዳ ዓመታዊ በጀቱ 150 ሚሊዮን አካባቢ ነው። የሠራተኛ [ደሞዝ] በጀቱ ግን ወደ 200 ሚሊዮን ይገባል” በማለት ላለው ከፍተኛ ወጪ ማሳያ ያነሳሉ።
ከዚህ ባለፈ ዞኑ ለአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ከበጀቱ ቀንሶ መክፈሉ እንዲሁም ከመጠን በላይ የሠራተኞች ቅጥር መፈጸሙ ችግሩን እንዳመጣው ኃላፊው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ችግሩ በተለይም “ገቢ የሌላቸው እና ወጪያቸው ከፍተኛ ነው” በተባሉ በስድስት ወረዳዎች ላይ የጎላ ነው የሚሉት አቶ መብራቱ፤ በዞኑ አስተዳደርም ገቢን በ75 በመቶ ማሳደግ እና ወጪውን መቀነስ እንደመፍትሄ ተይዟል ብለዋል።
ዞኑ ለገጠመው ችግር “ልዩ ዕቅድ” እንደነደፈ የተናገሩት ኃላፊው፤ በቅርብ ወራት ከችግሩ እንወጣለን በማለት ለሠራተኞች ተስፋ ሰጥተዋል።












