ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኬንያ እራሳቸውን አስርበው ሲፀልዩ የሞቱ ናቸው የተባሉ ሰዎች ቁጥር 47 ደረሰ
የኬንያ ፖሊስ የዓለም ፍጻሜ ተቃርቧል በሚል እራሳቸውን አስረበው ሲጸልዩ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉ ሰዎች አሃዝ 47 መድረሱን አስታወቀ።
ፖሊስ ቆፍሮ ካወጣቸው አስክሬኖች መካከል ሕጻናት የሚገኙበት ሲሆን፣ ተጨማሪ አስክሬኖች ሊገኙ እንደሚችሉ የአካባቢው ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ፖሊስ ከትኩስ የመቃብር ስፍራ የሰዎችን አስክሬን በቁፋሮ ያገኘው አንድ የሃይማኖት መሪ ነኝ የሚል ግለሰብ ለተከታዮቹ “የዓለም ፍጻሜ ተቃርቧል እየጾማችሁ የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትን ጠብቁ” ያላቸው ሰዎች እራሳቸውን ነጥለው ሲጸልዩ የሞቱ ሰዎች መገኝታቸውን ተከትሎ ምርመራ እያደረገ ባለበት ወቅት ነው።
ከአንድ ሳምንታት በፊት በኬንያ ምሥራቃዊ ክፍል ኪሊፊ በሚባለው የባሕር ዳርቻ ግዛት የ‘ጉድ ኒውስ ኢንትርናሽናል ቸርች’ አባላት መካከል አራቱ በረሃብ ሞተው እና በርካቶች ደግሞ እጅግ ተዳክመው ጫካ ውስጥ ተገኝተው ነበር።
ከቀናት በፊት ደግሞ ሻካሎሃ ተብሎ ከሚጠራው ጫካ ውስጥ 15 የቤተክርስቲያኗ አባላት የነበሩ ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል።
ፓስተር ማኬንዚ ንቴንጌ የተባለ የሃይማኖት ሰባኪ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ቢሆንም፣ በሰዎቹ ሞት ተጠያቂ አይደለሁም ሲል ይከራከራል። ይህ የሃይማኖት መሪ ‘ጉድ ኒውስ ኢንትርናሽናል ቸርች’ የተባለውን ቤተ-ክርስቲያን እአአ 2019 ላይ ዘግቻለሁ ይላል።
ይሁን እንጂ ግለሰቡ ተከታዮቹ ‘ኢየሱስን ማግኘት’ ከፈለጉ እራሳቸውን እንዲያስርቡ ነግሯቸዋል ተብሏል። ተከታዮቹም በተነገራቸው መሠረት የተባሉትን ካደረጉ በኋላ በረሃብ ሕይወታቸው አልፏል።
እስካሁን ድረስ ፖሊስ በጠቅላለው የ47 ሰዎች አስክሬንን አግኝቻለሁ ይበል እንጂ ክስተቱን ተከትሎ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በትክክል አልታወቀም።
የኬንያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኬቢሲ ግን 58 የመቃብር ቦታዎች ተለይተዋል ሲል ዘግቧል።
ፓስተር ማኬንዚ ከአንድ ሳምንት በፊት በቁጥጥር ሥር የዋለው እራሳቸውን አስርበው ሕይወታቸው ሳያልፍ አይቀርም የተባሉ የአምስት ሰዎች አስክሬን ከተገኘ በኋላ ነው።
ቪክተር ካኡዶ የተባሉ የአካባቢው ባለሥልጣን፤ “ወደ ጫካው ገብተን ግዙፍ ረዥም መስቀል ተተክሎ ስንመለከት በዚያ ቦታ የተቀበሩት ሰዎች አምስት ብቻ ሊሆን እንደማይችል አውቀናል” ብለዋል።
ለሰዎቹ ሞት ትክክለኛው መንስዔ ረሃብ መሆኑን ማረጋገጫ ለመስጠት ከአስክሬኖች ላይ የዘረ መል (ዲኤንኤ) ናሙና ተወስዶ ምርመራ እንደሚደረግ ነው ሲል 'ዘ ስታንዳርድ' የተባለው የኬንያ ጋዜጣ ዘግቧል።
ዘ ስታንደርስ በዘገባው ይህ ሰባኪ በአካባቢው ሦስት መንደሮችን ናዝሬት፣ ቤተልሄም እና ጁዴአ ብሎ ከሰየመ በኋላ ተከታዮቹን በውሃ ማቆሪያ ቦታዎች በማጥመቅ እንዲጾሙ አዟቸዋል ተብሏል።
ከእንዲህ አይነት የእምነት ሰባኪያን ምክር ጋር በተያያዘ በሚፈጸሙ የጾም እና ሌሎች ትዕዛዞች ምክንያት ምዕመናን በተለያዩ አገራት ጉዳት ሲደርስባቸው ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከሳምንታት በፊት ሞዛምቢክ ውስጥ አንድ ፓስተር እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀን እና ሌሊት እጾማለሁ ብሎ በመሞከሩ ክፉኛ ተጎድቶ ሆስፒታል ከገባ በኋላ ለሕልፈት መብቃቱ ይታወሳል።