ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን የደቀነችውን ስጋት ተከትሎ ለእስራኤል ‘የብረት አጥር’ እንሆናታለን ሲሉ ባይደን ገለጹ
ከፍተኛ ኢራናውያን አመራሮች የተገደሉበትን ጥቃት ተከትሎ ቴህራን የበቀል እርምጃ ልትወስድ ትችላለች የሚል ስጋት ባንዣበበት በአሁኑ ወቅት ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አሜሪካ ለእስራኤል “የብረት አጥር” ትሆናታለች ሲሉ ተናገሩ።
እስራኤል በሶሪያ የሚገኘውን የኢራን ቆንስላ ላይ ከሳምንት በፊት ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ኢራን “ከፍተኛ ጥቃት ልትፈጽም” እያስፈራራች ነው ሲሉ ባይደን አስጠንቅቀዋል።
“የእስራኤልን ደኅንነት ለመጠበቅ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲሉም ፕሬዝዳንቱ አክለዋል።
እስራኤል ሶሪያ ደማስቆ ውስጥ በቆንስላ ጽህፈት ቤቷ ላይ ያደረሰችው ጥቃት በኢራን ግዛት ላይ ከደረሰ ጥቃት ጋር እኩል ነው ሲሉ ረቡዕ ዕለት የኢራኑ መሪ ተናግረዋል።
አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በቴሌቭዥን በተሰራጨው ንግራቸው “በቆንስላችን ላይ ጥቃት ሰነዘሩ ማለት ግዛታችንን አጠቁ እንደማለት ነው” ብለዋል።
“ክፉው አገዛዝ መቀጣት አለበት፤ ይቀጣልም” ሲሉ ዝተዋል።
ነገር ግን አገራቸው ምን ዓይነት የበቀል ጥቃት እንደምትወስድ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
ኢራን እስራኤልን በቀጥታ ብታጠቃ ግጭቱ የበለጠ የከፋ አደጋ ሊያመጣ ይችላል ተብሏል። እንደ ተንታኞች ከሆነም ኢራን ግጭት ውስጥ ለመግባት የሚሆን ወታደራዊ አቅም የላትም።
አማራጭ ሊሆን የሚችለው በጎረቤት ሊባኖስ ያሉ እንደ ሂዝቦላህ ባሉ ታጣቂዎች አማካይነት በእስራኤል ላይ ትንንሽ ጥቃቶችን መፈጸም ነው።
ኢራን እስራኤልን ላይ የሳይበር ጥቃት ልታደርስ እንደምትችልም ባለሙያዎች ጠቁመዋል።
ከቀናት በፊት በኢራን ቆንስላ ላይ በደረሰ ጥቃት የኢራን ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችን ጨምሮ 13 ሰዎች ተገድለዋል።
እስራኤል ለጥቃቱ ኃላፊነት ባትወስድም ከጥቃቱ ጀርባ እንደነበረች ግን በሰፊው ተነገሯል።
በቀጠናው ያሉ የአሜሪካ እና የእስራኤል ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲቆሙም ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ ጋር በዋይት ሐውስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ነው።
“ለጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እንደነገርኩት ከኢራን እና ተላላኪዎቿ ለሚሰነዘረው ጥቃት ለእስራኤል የብረት አጥር እንሆናታልን። አሁንም ልድገውም የብረት አጥር እንሆናታለን” ብለዋል ባይደን።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ ካቀረቡ እና በኔታንያሁ የጦርነት ስትራቴጂ እንደማይስማሙ ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ከሳምንት በፊት ከዩኒቪዥን ከተባለ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “እሱ እያደረገ ያለው ነገር ስህተት ይመስለኛል። በእሱ አካሄድ አልስማማም” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት እስራኤል በጋዛ ሰባት የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ላይ የፈጸመችውን ግድያ ተከትሎ በባይደን እና በኔታንያሁ መካከል ውጥረት የተሞላበት የስልክ ንግግር ከተደረገ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለኢራናውያን መልዕክት ለማስተላለፍ እየሞከሩ ነው። ባይደን እና ኔታንያሁ መካከል የሃሳብ ልዩነት ቢኖርም፣ በእስራኤል ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት የአሜሪካን አስከፊ ምላሽ ይገጥመዋል የሚል ነው መልዕክቱ።
ውጥረቱን ለማርገብ በሚል የሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ የኳታር እና የኢራቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዚህ ሳምንት ከኢራን አቻቸው ጋር መነጋገራቸውን አክሲዮስ ዘግቧል።
ሚኒስትሮቹ ውጥረቱን ለማርገብ ከባይደን የመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ አማካሪ ብሬት ማክጉርክ መልዕክት እንዲያስተላልፉ ተጠይቀዋል።