ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአውሮፓ ህብረት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ያላገኙ ስደተኞች በግዳጅ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን የሕግ ማሻሻያ አጸደቀ
ከዓመታት ድርድር በኋላ የአውሮፓ ፓርላማ የህብረቱን የስደተኞች እና የጥገኝነት ደንቦችን የሚያጠናክር ትልቅ ማሻሻያ አጸደቀ።
የአውሮፓ ህብረት የጥገኝነት እና የፍልሰት ስምምነት ከ2015 ጀምሮ ሲመከርበት የቆየ ሲሆን በሁለት ዓመት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
አዲሱ ሕግ የጥገኝነት ሂደትን ለማፋጠን እና መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞች ደግሞ ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ለመጨመር የታለመ ነው።
አዲሱ ሕግ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት የጥገኝነት ጠያቂዎችን ኃላፊነት እንዲጋሩም ያደርጋል።
ባለፈው አመት 380 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች የአውሮፓ ህብረትን ድንበር በህገ ወጥ መንገድ አቋርጠዋል። ይህም እአአ ከ 2016 ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው ተብሏል።
የአውሮፓ ህብረት ስምምነቱ በአባል አገራት መካከል ያለውን "የጋራ ግዴታ"እና ከተለዋዋጭ ኃላፊነት ያጣመረ ነው ብሏል።
ምንም እንኳን አንዳንድ የአውሮፓ ህብረት አገራት የተወሰኑ የስምምነቱን ክፍሎች ቢቃወሙም በሚያዝያ ወር መጨረሻ በሚደረግ ድምጽ አሰጣጥ የአብዛኛውን ይሁኝታ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በቀረበው ሕግ መሰረት የአውሮፓ ህብረት 27 አባል አገራት በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከጣሊያን፣ ግሪክ እና ስፔን ካሉ "የድንበር" አገራት እንዲወስዱ ወይም በምትኩ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቀርቡ ይጠበቅባቸዋል።
በአዲሱ ስምምነት መሠረት "ዝቅተኛ ተቀባይነት የማግኘት እድል" ያላቸው የጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አውሮፓ ህብረት ግዛት ሳያስገቡ ጉዳያቸው በፍጥነት መታየት አለበት ይላል።
ስምምነቱ በተጨማሪም የጥገኝነት ጥያቄዎችን ቢበዛ በ12 ሳምንታት ውስጥ ለመጨረስ ያለመ ነው። የጥገኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው ደግሞ በተመሳሳይ 12 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በግዳጅ ወደ አገራቸው መመለስ አለባቸው።
ስደተኞች ከመግባታቸው በፊት ባሉ በሰባት ቀናት ውስጥ ጠንከር ያለ የማጣራት ሂደት ይደረግላቸዋል። ይህም የመለየት፣ የጤና እና የደህንነት ፍተሻዎችን ይጨምራል ተብሏል።
ከስድስት ዓመት እና በላይ ለሆኑ ማናቸውም ስደተኞች የባዮሜትሪክ መረጃ ይሰበሰባል ተብሏል። ስደተኞች ቁጥር በአጋጣሚ ካሻቀበም ምላሽ የሚሰጥበት አሠራር ተዘርግቷል።
የስደተኞች ስምምነት በሁለቱ ዋና ዋና የፖለቲካ ቡድኖች የተደገፈ ነው ተብሏል። እነዚህም የአውሮፓ ፒፕልስ ፓርቲ ግሩፕ እና ፕሮግሬሲቭ አሊያንስ ኦፍ ሶሻሊስት ዴሞክራት ናቸው።
ሁለቱም ቡድኖች በሰኔ ወር በሚካሄደው የፓርላማ ምርጫ ሊኖር የሚችለውን ጠንካራ ተቃውሞ ለማለፍ ከወዲሁ እየጣሩ ነው።
የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልስ “ታሪካዊ እና አስፈላጊ እርምጃ” ሲሉ አወድሰውታል። የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤታ ሜሶላ በበኩላቸው “በአብሮነት እና በኃላፊነት መካከል ያለውን ሚዛን” ጠብቋል ብለዋል።
"ሁሉንም ነገር በአንድ ጀምበር ባይፈታም ግን 10 ግዙፍ እርምጃ የተጓዘ ነው" ሲሉ አወድሰውታል።
ምንም አይነት የስደት ስምምነት ቢደረስም ሃንጋሪ መደበኛ ያልሆኑ ስደተኞችን እንደማትወስድ አቋሟን አንጸባርቃለች። እና የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ በበኩላቸው የተወሰኑ ጥገኝነት ጠያቂዎችን መውሰድ አልያም ለድንበር አገራት ገንዘብ መክፈል የሚለውን ሃሳብ "ተቀባይነት የሌለው" ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
ምንም እንኳን በርካታ አውሮፓ ፓርላማ አባላት ሕጉን ቢቀበሉትም፤ ብዙዎች ደግሞ ስምምነቱ “ፍጹም” አለመሆኑን ጠቁመዋል።
የስሎቫንያ አወውሮፓ ፓርላማ አባል ማትያዝ ኔሜክ “ልንሰራበት የምንችለው ስምምነት ነው” ብለውታል። የቤልጂየሟ ሂልዴ ቮትማንስ በበኩላቸው ህጉ “ፍፁም አይደለም” ካሉ በኋላ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡት ግን አሳውቀዋል።
የግራ ዘመም እና የቀኝ ዘመም ቡድኖች ስምምነቱን ተቃውመዋል።
የፈረንሣዩ ቀኝ አክራሪ ናሽናል ራሊ አባል ጆርዳን ባርዴላ ስምምነቱ “አስፈሪ” ነው ብለውታል። አውሮፓውያን ስምምነቱን የደገፉትን ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንን በመቃወም በመጪው ሰኔ በሚካሄደው የአውሮፓ ምርጫ ላይ ድምጽ እንዲሰጡም አሳስበዋል።
ድምጽ በሚሰጥበት ወቅት ተቃዋሚዎች "ስምምነቱ ገዳይ ነው። አይሆንም" በማለት እና የወረቀት አውሮፕላኖችን በመወርወር ማወካቸው ታውቋል::
በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የአውሮፓ ፓርላማ አባላት ማሻሻያውን እንዲቃወሙ አሳስበዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስምምነቱ በበኩሉ ስምምነቱ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ “ከፍተኛ ስቃይ” የሚመራ ሲል አስጠንቅቋል።
ከመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚነሳው አንድ ተቃውሞ ዝቅተኛ ተቀባይነት የሚኖራቸው ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳያቸው በድንበር መግቢያዎች ወይም በማቆያ ስፍራዎች እንዲስተናገዱ በማድረግ ፍትሃዊ ዕድል የማግኘት ተስፋቸውን ያመነምነዋል የሚል ነው።