ትራምፕ "እያሴሩብኝ ነው" ያሏቸው የቻይና፣ የሩሲያ እና የሰሜን ኮሪያ መሪዎች የፈጠሩት ግንባር

የቻይና፣ የሩሲያ እና የሰሜን ኮሪያ መሪዎች ቤይጂንግ ባዘጋጀችው ወታደራዊ ትርዒት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ ሆነው ለሕዝብ ታዩ።

ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ግዙፍ እና ዘመናዊ የጦር መሳያዎችን ለትርዒት ባቀረቡበት በዓል ላይ "ዓለም የሰላም እና የጦርነት አማራጮችን ፊት ለፊት ተጋፍጣለች" ሲሉ ተናግረዋል።

ቻይና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓን ላይ ድል የተቀዳጀችበትን 80ኛ ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ ባዘጋጀችው ታላቅ ወታደራዊ ትዕይንት ላይ አህጉር አቋራጭ መሳሪያዎችን ለዕይታ አቅርባለች።

የጦር መሳርያ ትዕይንቱ ቻይና ምን ያህል በቴክኖሎጂ ርቃ መጓዟን ወይንም የት እንደደረሰች የሚያሳይ ሳይሆን አገሪቱ ወዴት እየሄደች እንደሆነ የሚያመለክት ነው ተብሏል።

ዢ በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ሁለት መሪዎች፣ የሩሲያው ቭላድሚር ፑቲን እና የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ጎን የቆሙ መሪ ሆነዋል።

እንዲሁም መከላከያቸው የምዕራቡን ዓለም ተግዳሮት ለመቋቋም የተዘጋጀ መሆኑንም ለማሳየት ችለዋል።

ወታደራዊ ትርዒቱ ኃይልን፣ አርበኝነትን ለማሳየት በሚገባ የተደራጀ ነበር።

ረቡዕ፣ ነሐሴ 28/ 2017 ዓ.ም. በቀረበው ትዕይንት ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እንዲሁም የጦር መሳሪያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የቻይና ጦርን የማዘመን ፕሮግራም አሳይተዋል።

ነገር ግን በትርዒቱ ወቅት አይረሴ የሆነው አንድ ቅጽበት የተፈጠረው የመጀመሪያው መድፍ ከመተኮሱ በፊት ነው።

ፕሬዝዳንት ዢ የሰሜን ኮሪያውን ኪም እጅን ጨብጠው እንኳን ደህና መጣህ ካሉ በኋላ ፑቲንን ሰላም ብለዋል። ከዚያም ሦስቱም መሪዎች በጋራ በመሆን ወደ ወታደራዊ ትርዒቱ አምርተዋል።

ሦስቱ ፕሬዝዳንቶች በጋራ እንዲህ ሲታዩ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን፣ እነርሱም ቅጽበቱን በሚገባ ተጠቅመውበታል።

በኋላ ላይ በነበረ የጎንዮሽ ውይይት ኪም እና ፑቲን ተገናኝተው ፒዮንግያንግ ወታደሮቿን በዩክሬን ጦርነት ላይ እንዲሳተፉ በመላኳ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ፑቲን እና ኪም ከ24 አገራት ሌሎች መሪዎች ጋር በቤይጂንግ የተዘጋጀውን ወታደራዊ ትርዒት ታድመዋል።

የቻይና የቀድሞ መሪዎች በታያናንሜን ተገኝተው ወታደራዊ ትርዒቱ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሁ ጂንታኦ ግን በስፍራው አልነበሩም።

የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሊ ጄይ ሚዩንድ የተጋበዙ ቢሆንም ሳይገኙ ቀርተዋል።

ፕሬዝዳንት ዢን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ያገኙት የሕንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እንዲሁ በበዓሉ ላይ አልተገኙም።

በወታደራዊ ትርዒቱ ላይ ከተገኙ የዓለም መሪዎች መካከል የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሶድ ፔዜሽኪያን፣ የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼባዝ ሻሪፍ፣ የቬትናሙ ሉዎንድ ቹንግ እንዲሁም የዚምባብዌው ኤመርሰን ምናንንጋግዋ ይገኙበታል።

በርካታ የምዕራቡ ዓለም መሪዎች የቻይናን "የድል ቀን" ወታደራዊ ትርዒት ሳይታደሙ ቀርተዋል።

የስሎቫኪያው ሮበርት ፊኮ እና የሰርቢያው አሌክሳንደር ቩቺች በበዓሉ ላይ ተገኝተው ከፑቲን ጋር ፎቶ ተነስተዋል።

በቤጂንግ ቲያንሜን አደባባይ በተካሄደው ሠልፍ ላይ ወደ 50,000 የሚጠጉ ቀደም ብሎ በጥንቃቄ የተመረጡ ታዳሚዎች ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንት ዢ ከተለያዩ የቻይና መከላከያ ክፍሎች ተመርጠው በቻንጋን አደባባይ የተገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን ጎብኝተዋል።

ጨረር የሚጠቀሙ መሳሪያዎች፣ ድሮኖች፣ ሮቦት እንዲሁም ግዙፍ ሠርጓጅ የኒውክሌር ድሮኖች በትርዒቱ ላይ ለዕይታ ከቀረቡት መካከል ናቸው።

ቻይና "ሎያል ዊንግ ማን' ስትል የሰየመችውን ስውር ጥቃት የሚፈጽም ድሮኗን ለዕይታ ያቀረበች ሲሆን፣ ጥቃት በሚፈጸምበት ወቅት በሰው ከሚበርሩ የጦር ጀቶች ጎን ለጎን በመብረር እገዛ ማድረግ ይችላሉ ተብሏል።

በቲያናንሜን አደባባይ ላይ የቀረበው ወታደራዊ ትርዒቱ ሲያበቃ በሺህዎች የሚቆጠሩ እርግቦች እና ፊኛዎች ወደ አየር ተለቅቀዋል።

ተጋባዥ እንገግዶች የምሳ ግብዣ የተደረገላቸው ሲሆን፣ፕሬዝዳንት ዢ ዓለም "ወደ ጫካ ሕግ ፈጽሞ መመለስ የለባትም" ሲሉ ጽዋቸውን አንስተዋል።

ፕሬዝዳንቱ አምስት ደቂቃ በፈጀው ንግግራቸው ወቅት የትኛውንም የምዕራቡን ዓለም በስም ጠርተው ያልተናገሩ ቢሆንም የቻይና ባለሥልጣናት ቀደም ሲሉ አሜሪካን የዓለም አገራት ላይ ታሪፍ መጣሏን ተከትሎ "ዘላፊ" ብለዋት ነበር።

ዢ አክለውም "ሁሉም አገራት ለሰው ልጆች የወደፊት ብሩህ ሰብዓዊነት ለመፍጠር እንዲሁም ሰላም እና አብሮ መሥራትን ጨምሮ . . . ከታሪክ ይማራሉ ብለን በጽኑ እናምናለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም "ለሁሉም የሰው ልጆች የጋራ ብልጽግና" ሲሉ ጽዋቸውን አንስተዋል።

ከዚህ በኋላ ፑቲን እና ኪም ለሁለት ሰዓት ከግማሽ የቆየ የሁለትዮሽ ምክክር አድርገዋል።

ሁለቱ መሪዎች ሰሜን ኮሪያ በዩክሬን ጦርነት ላይ ስላበረከተችው አስተዋጽኦ እንዲሁም ባለፈው ሰኔ ወር በሁለቱ አገራት መካከል ከስምምነት ስለተደረሰባቸው ጉዳዮች ተወያይተዋል።

15,000 የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች፣ ሩሲያ በዩክሬን የምታካሄደው ጦርነት ላይ ተሳትፈዋል ተብሎ ይታመናል።

ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ጦር መሳሪያ የምታቀርብ ሲሆን፣ በምላሹ ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ማበልፀግ ድጋፍ ታገኛለች ተብሎ ይታመናል።

የቻይናው ወታደራዊ ትርዒት የጦር መሳሪያዎች እና ወታደሮች ማሳያ ብቻ ሳይሆን የሦስቱ መሪዎች ዢ፣ ኪም እና ፑቲን ተገናኝቶ መወያያ የነበረ ሲሆን የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትኩረትንም መሳብ ችሏል።

በወታደራዊ ትርዒቱ ላይ ያልተገኙት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ፕሬዝዳንት ዢ ከሩሲያ እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር በመሆን አሜሪካ ላይ እያሴሩ ነው ሲሉ ተችተዋቸዋል።

"አሜሪካ ላይ እያሴራችሁ እያለ ለቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኡን ሰላምታዬን አድርስልኝ" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዩሪ ኡሻኮቭ "አሜሪካ ላይ ምንም ዓይነት ማሴር አልነበረም" ሲሉ መናገራቸውን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ኡሻኮ የትራምፕን ጽሑፍ "አስገራሚ" በማለት ፑቲን፣ዢ እና ኪም "አሜሪካ ላይ ሴራ እንኳን እያሰቡ አልነበረም" ካሉ በኋላ ሦስቱ መሪዎች ዋሺንግተን "አሁን ባለው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ላይ ያላትን ሚና ይገነዘባሉ" ብለዋል።