ትራምፕ የቻይናው መሪ ከፑቲን እና ከኪም ጋር በአሜሪካ ላይ እያሴሩ ነው ሲሉ ከሰሱ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይና አቻቸው ሺ ጂንፒንግ ከሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ መሪዎች ጋር በጥምረት በአሜሪካ ላይ እያሴሩ ነው ሲሉ ወቀሱ።

ትራምፕ ይህንን ያሉት ቻይና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጃፓን ድል የተቀዳጀችበትን 80ኛ ዓመት መታሰቢያ አስመልክቶ ታላቅ ወታደራዊ ትዕይንት ረቡዕ፣ ነሐሴ 28/ 2017 ዓ.ም ማካሄዷን ተከትሎ ነው።

በዚህ ታላቅ የወታደራዊ በዓል የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡንን ጨምሮ 26 መሪዎች ተገኝተዋል።

ትራምፕ ለፕሬዚዳንት ሺ "በአሜሪካ ላይ በጋራ እያሴራችሁ ላላችሁት ለቭላድሚር ፑቲን እና ለኪም ጆንግ ኡን ሞቅ ያለ ሰላምታ አቅርብልኝ" ሲሉ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘ ማህበራዊ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ትራምፕ ከዚህ ቀደም በቻይና፣ ሩሲያ እና ሌሎች አገራት መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአሜሪካ ተግዳሮት ጋርጧል መባሉን አጣጥለው ነበር።

ትራምፕ በዚሁ የማህበራዊ ገጽ ልጥፋቸው ላይ አሜሪካ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለቻይና የሰጠችውን ከፍተኛ "መስዋዕትነት" አውስተዋል።

"በርካታ አሜሪካውያን ለቻይና ድል እና ክብር ሲሉ ሞተዋል። ለጀግንነታቸው እና መስዋዕትነታቸው በትክክል እንደተከበሩ እና እንደሚታወሱ ተስፋ አድርጋለሁ" ብለዋል።

ትራምፕ አገራቸው ያጋጠማትን የንግድ ሚዛን ጉድለት አስተካክላለሁ በሚል ታሪፍ መጣላቸውን ተከትሎ ከቻይና ጋር ወደ ንግድ ውጥረት ገብተዋል።

ትራምፕ የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅምና ኢንዱስትሪ ለመጠበቅ ታሪፉ ወሳኝ ነው ያሉ ሲሆን ይህም በመላው አለም የምጣኔ ኃብትና ፖለቲካዊ ቀውስ አድርሷል።

ትራምፕ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ማንኛውንም የዲፕሎማሲ ዋጋ ለመክፈል ፈቃደኛ ሆነዋል።

ትራምፕ ወደ አሜሪካ በሚገቡ በበርካታ አገራት ምርቶች ላይ ታሪፍ ሲጥሉ በከፍተኛ ሁኔታ የተመታችው ቻይና ነበረች።

ቻይናም በአጸፋው በአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ የጣለች ሲሆን፤ ይህም አገራቱ እርስ በርስ የጣሉትን ታሪፍ 145 በመቶ እንዲያሻቅብ አድርጎታል።

ግንቦት ወር ላይ በስዊትዘርላንድ በተካሄደ ውይይት ሁለቱ አገራት ጊዜያዊ እርቅ ላይ ደርሰው ነበር።

በዚህም ውይይት አሜሪካ በቻይና ላይ የጣለችው ታሪፍ ወደ 30 በመቶ ዝቅ እንዲል እንዲሁም ቻይና በአሜሪካ ላይ የጣለችው ወደ 10 በመቶ እንዲሆን ተስማምተዋል።

በተጨማሪም ወሳኝ የሆኑ ማዕድናት ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ ጊዜያዊ እርቅ ላይ ደርሰዋል። ሁለቱም አገራት በዚህ እርቅ መሠረት የንግድ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ የ90 ቀናት ገደብ ተቀምጦ ነበር።

ነገር ግን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሁለቱም አገራት ከታሪፍ ውጪ የተገቡ ቃሎችን በመጣስ ተወነጃጅለዋል።

ቻይና እና አጋሮቿ አሜሪካን ለመገዳደር አለም አቀፍ ጥምረት ለመፍጠር እየሞከሩ እንደሆነ ከቢቢሲ በቅርቡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ትራምፕ ሲመልሱ "አይሆንም፤ ቻይና ትፈልጋነለች" ብለዋል።

አክለውም "እንደምታውቁት እኔ ከፕሬዚዳንት ሺ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለኝ። ቻይና ከኛ በላይ ትፈልገናለች። ይህ በፍጹም አይታየኝም" ብለው ነበር።

ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ከአንድ የአሜሪካ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሩሲያ እና በቻይና መካከል የሚፈጠረው ጥምረት እንደማያሳስባቸው ተናግረው ነበር።