የሩሲያ ከፍተኛ የጦር መኮንን ላይ ተኩስዋል የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎች ተለዩ

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሩሲያ ከፍተኛ የጦር መኮንን የሆኑት ሌተናንት ጀነራል ቭላድሚር አሌክሲዬቭ ላይ ተኩሰዋል የተባሉ ሦስት ተጠርጣሪዎች መለየታቸውነ ተገለጸ።

ጥቃቱን ፈጽሟል የተባለው ዩክሬን የተወለደው ሩሲያዊ ሉያምቦር ኮርባ ነው።

የሩሲያ የመርማሪዎች ኮሚቴ እንዳለው ግለሰቡ ታኅሣሥ ላይ ሞስኮ የገባው ከዩክሬን የደኅንነት ተቋም "የሽብር ድርጊት እንዲፈጽም" ተልዕኮ ተሰጥቶት ነው።

ዩክሬን በጥቃቱ እጇ እንደሌለ በመግለጽ ክሱን አስተባብላለች።

የ64 ዓመቱ የጦር መኮንን ያለፈው ሳምንት አርብ በመኖሪያ ሕንጻ አካባቢ ከተተኮሰባቸው በኋላ በሰሜን ምዕራብ ሞስኮ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ቀዶ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ከሰመመን መንቃታቸውን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የሩሲያ ወታደራዊ የስለላ ተቋም ሁለተኛው እርከን ላይ የሚገኙ የጦር መኮንን ናቸው።

ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጥቃት የተፈጸመባቸው ከፍተኛ አመራር መሆናቸው ተገልጿል።

ቃል አቀባይ ስቪትላና ፔትሬንኮ እንደተናገሩት ጥቃቱን ያደረሰው ግለሰብ ወደ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ተጉዟል። ከዚያም በሰዓታት ውስጥ ለሩሲያ ተላልፎ ተሰጥቷል።

የሩሲያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ ሩ-24 ተጠርጣሪው በፀጥታ ኃይሎች ታጅቦ ከአውሮፕላን ሲወርድ የሚያሳይ ቪድዮ አስተላልፏል።

ቃል አቀባዩዋ "መርማሪዎች ጥቃት የተፈጸመበትን ሥፍራ ቃኝተዋል። ማካሮቭ ሽጉጥ ከድምጽ ማፈኛ ጋር እንዲሁም ሦስት ጥይትም በቦታው አግኝተዋል" ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያንን ተጠርጣሪው እንዲያዝ ላደረጉት ትብብር ማመስገናቸው ተዘግቧል።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንደሪይ ሳቢሃን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ዩክሬን ጦርነቱን ለመግታት የሚደረገውን ውይይት ማሰናከል ስለማትሻ ጥቃቱን አልፈጸመችም።

የሩሲያ ወታደራዊ የስለላ ተቋም ኃላፊ አድም ኢጎር ኮስታዩኮቭ በአቡ ዳቢ እየተካሄደ ባለው ውይይት የሚሳተፈውን የአገራቸውን ልዑካን ቡድን ይመራሉ።

በውይይቱ ዩክሬን እና አሜሪካም እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የዋነኛው ተጠርጣሪ አባሪ ነው የተባለው ግለሰብ ቪክቶር ቫሲን እንደሚባል ይፋ ተደርጓል። በቁጥጥር ሥር ውሎም ክስ ተመስርቶበታል።

ሦስተኛዋ ተጠርጣሪ ዚናይዳ ሰርብሪክያ እንደምትባል እና ወደ ዩክሬን እንደሸሸች ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም ዩክሬን ከፍተኛ የሩሲያ የጦር አመራሮች ላይ ጥቃት አድርሳለች። ሩሲያም በምላሹ ከየዩክሬን ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ላይ እርምጃ መውሰዷ አይዘነጋም።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2024 ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ የተባለ የጦር መሪን በመግደል የዩዝቤኪስታን ዜጋ መታሰሩ ይታወሳል።

የዩክሬን የስለላ ተቋም አመራር ተተኩሶባቸው መገደላቸውን ተከትሎ ከአገሪቱ የጦር ዕዞች የአንዱ ኮማንደር ሸርሊ ፊሞኖቭ ላይ የተቃጣ ጥቃት መቀልበሱ ተገልጾ ነበር።