የዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ከኃላፊነታቸው ሊለቁ ነው

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ማይክ ዋልዝ እና ምክትላቸው አሌክስ ዎንግ ከኃላፊነታቸው ሊለቅቁ መሆኑን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

በአሜሪካ የቢቢሲ የሚዲያ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እና ምክትላቸው ከኃላፊነታቸው ሊለቅቁ ነው።

የዶናልድ ትራምፕ ዋና የደኅንነት አማካሪ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቅቁ የተሰማው በየመን የታቀደ የአየር ጥቃትን በሚመለከት በሲግናል የማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በከፈቱት ቡድን ውስጥ በስህተት አንድ ጋዜጠኛ እንዲካተት ማድረጋቸውን በሚመለከት ኃላፊነት ከወሰዱ በኋላ ነው።

ማይክ ዋልዝ ጋዜጠኛ ባለበት የሲግናል ቡድን ውስጥ በየመን ላይ ለመፈጸም የታቀደ ወታደራዊ ጥቃትን በተመለከተ መረጃ በማጋራታቸው ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር።

ይህ የሲግናል ቡድን ብሔራዊ ምሥጢርን ባለሥልጣናት የሚለዋወጡበት ሲሆን፣ ጋዜጠኛው ቡድኑን መቀላቀሉን ዋይት ሐውስ በወቅቱ አረጋግጦ ነበር።

የ51 ዓመቱ ማይክ ዋልዝ መጋቢት ወር ላይ በሲግናል ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የብሔራዊ ደኅንነት ጉዳይን በተመለከተ የትራምፕ አስተዳደር አማካሪዎችን አካትተው በከፈቱት ቡድን ውስጥ የ'ዘ አትላንቲክ' መጽሔት ጋዜጠኛ በስህተት መካተቱ ከተሰማ በኋላ በርካታ ትችት ቀርቦባቸዋል።

የትራምፕ አስተዳደር አባላት በወቅቱ በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ምስጢራዊ መረጃ አልተጋረም እንዲሁም የደኅንነት አደጋ የለውም ሲሉ ጉዳዩን አጣጥለውት ነበር።

የ'ዘ አትላንቲክ' መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጄፍሪ ጎልድበርግ እንዳለው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴት የሚገኙበት ቡድን ውስጥ ነበር ሳያውቀው የተካተተለው።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በጥቂት ወራት ውስጥ ከአስተዳደራቸው አንድ ኃላፊ ሲለቅቁ ይህ የመጀመሪያው ነው።

ሮይተርስ የዜና ወኪል በጉዳዩ ላይ ገለጻ የተደረገላቸው አራት ሰዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ማይክ ዋልዝ ከኃላፊነታቸው እንዲለቅቁ ጫና ተደርጎባቸዋል።

የዋልዝን ቦታ ማን አንደሚተካው እስካሁን ግልጽ ባይሆንም በዩክሬን እና በሩሲያ ጦርነት እንዲያበቃ እያደራደሩ የሚገኙት የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተገምቷል።

የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ ከሮይተርስ ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም። ቢቢሲ ከዋይት ሐውስ በጉዳዩ ላይ ማብራርያ ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

የደኅንነት አማካሪው እና የረዳታቸው ከኃላፊነታቸው መነሳት የተሰማው ዶናልድ ትራምፕ በዋይት ሐውስ 100 የሥልጣን ቀናትን ማስቆጠራቸውን እያከበሩ በሚገኙበት ወቅት ነው።

ባለፈው መጋቢት ወር የ'ዘ አትላንቲክ' መጽሔት ዋና አዘጋጅ ጄፍሪ ጎልድበርግ በስህተት በሲግናል የውይይት ቡድን ውስጥ ከከፍተኛ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር መካተቱን ገልጾ ነበር።

በዚህ የሲግናል ቡድን ውስጥ ማይክ ዋልዝ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ፒት ሄግሴዝ እንዲሁም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ የነበሩ ሲሆን፣ በየመን ስለሚፈጸም የአየር ጥቃት ውይይት እያደርጉ ነበር ተብሏል።

ጎልድበርግ ቡድኑን እንዲቀላቀል ያደረጉት የደኅንነት አማካሪው ማይክ ዋልዝ መሆናቸውን የገለፀ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ስህተት መሥራታቸውን አምነዋል።

በወቅቱ ትራምፕ እንዲሁም የአሜሪካ ደኅንነት ኃላፊ ክስተቱ የደኅንነት አደጋ የለውም ሲሉ ጉዳዩን ያጣጣሉ ሲሆን፣ ምሥጢራዊ ሰነድም አለመጋራቱን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዋልዝ "ፍፁም ባልሆነ መሳሪያ እና ቴክኖሎጂ በተገቢው ሁኔታ እየሠራ ነው" ሲሉ ተከላክለው ነበር።

ይኹን እንጂ የተወሰኑ የዲሞክራት እና ሪፐብሊካን አባላት በርካታ እና የሕግ ባለሙያዎች ጥሰት ተፈጽሟል ሲሉ የጠሩት ክስተት ላይ ምርመራ እንዲካሄድ ሲወተውቱ ነበር።