ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የ14 ዓመት ታዳጊ መገደሉን ተከትሎ አልባንያ ቲክቶክን ለዓመት ልታግድ ነው
የ14 ዓመት ታዳጊ በስለት ተወግቶ መገደሉን ተከትሎ አልባንያ ለአንድ ዓመት ቲክቶክን እንደምታግድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሩ።
ባለፈው ወር ታዳጊው ከተገደለ በኋላ ማኅበራዊ ሚዲያ ልጆች ላይ የሚያሳድረው ጫና ስጋት ፈጥሯል።
ጠቅላይ ሚኒስት ኤዲ ራማ እንዳሉት ቲክቶክ ለአንድ ዓመት ይታገዳል።
ቲክቶክ ከአልባንያ በአፋጣኝ ማብራሪያ እፈልጋለሁ ብሏል።
የ14 ዓመቱን ታዳጊ የገደለው ሰውም ይሁን ታዳጊው ቲክቶክ እንዳላቸው ማረጋገጫ እንዳልተገኘ ቲክቶክ ለቢቢሲ ገልጿል።
በአልባንያ መዲና ቲራና መምህራን፣ ወላጆችና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች በተገኙበት ውይይት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቲክቶክ "የሰፈር ወሮበላ ነው" ነው ብለዋል።
"ለአንድ ዓመት ቲክቶክ እናግዳለን። ወላጆች የልጆቻቸውን የትምህርት ዕድገት የሚከታተሉበት አሠራር እንዘረጋለን" ሲሉም አክለዋል።
በደቡባዊ ቲራና ትምህርት ቤት አቅራቢያ በተነሳ ድብድብ ታዳጊው ሲሞት ሌላ ታዳጊ ተጎድቷል።
ፀቡ የተጀመረው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነው ተብሏል።
መምህራን፣ ወላጆችና የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ስለማኅበራዊ ሚዲያ ውይይት ማድረግም ጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በቻይና ቲክቶክ የሚያገለግለው ለልጆች ትምህርት፣ ለተፈጥሮ ጥበቃና ባህልን ለመጠበቅ ነው። ከቻይና ውጭ ያለው ቲክቶክ ግን ርካሽና አሳሳች ነው። ይሄን ለምን እንፈልጋለን ታዲያ?" ብለዋል።
የቲክቶክ ዋነኛ ገበያ በሆችው ሕንድም መተግበሪያው ታግዷል።
በኢራን፣ ኔፓል፣ አፍጋኒስታንና ሶማሊያም ቲክቶክ ታግዷል።
በአሜሪካ ምክር ቤት ቲክቶክ የማይሸጥ ከሆነ እንዲታገድ የተላለፈውን ውሳኔ ቲክቶክ እየታገለ ነው።
አሜሪካ ቲክቶክ ከቻይና መንግሥት ጋር ትስስር አለው በሚል ሲሆን ለማገድም የምትፈልገው ቲክቶክና ባለቤት ተቋሙ ማይትዳንስ ይህንን ያስተባብላሉ።
ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ቤልጄምን ጨምሮ ብዙ የአውሮፓ አገራት የልጆች ማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ገደብ ጥለዋል።
አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ያሉ ልጆች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ አግዳለች።
የዩኬ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጸሐፊ ፒተር ካይል ከ16 ዓመት በታች ያሉ ልጆች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያግድ ሕግ ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።