ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲስ አበባ ጉብኝት ያደረጉት የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማኽሮን ምን አሉ?
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማኽሮን በኢትዮጵያ የአንድ ቀን ኦፊሴላዊ ጉብኝት አድርገው ተመልሰዋል።
ማኽሮን ኢትዮጵያ ሲደርሱ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ማኽሮን በሁለቱ ሀገራት የጋራ ትብብር እንዲሁም በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የፈረንሳይ መንግሥት ብሔራዊ ቤተ-መንግሥቱን ለማደስ እንዲሁም ለላሊበላ ውቅር ዐቢያተ ክርስትያናት ጥገና ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀዋል።
ማኽሮን በበኩላቸው በኤክስ ገፃቸው በአማርኛ በፃፉት መልዕክት "በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት በታሪክ እና በጋራ ፕሮጀክቶች ላይ የተመሠረተ ነው" ብለዋል።
አክለው በላሊበላ እየተሠራ ያለው የቅርስ ጥበቃ ፕሮጀክት በቅርብ ወራት እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው የብሔራዊ ቤተ መንግሥት እድሳት ፕሮጀክትም "ዛሬ የሚያኮራ እውነታ ሆኖ እየታየ" መሆኑን ጠቅሰዋል።
ማኽሮን አክለው ሀገራቸው ፈረንሳይ "የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዘመንን ለመደገፍ እና በትግራይ የሰላምና የመረጋጋት መሰረት የሆነውን የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ" ትብብር እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።
ሁለቱ መሪዎች ቅዳሜ ዕለት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማኽሮን ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በውይይት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
ማኽሮን ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የገቡትን የአንካራ ስምምነት አወድሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ በቱርኩ ፕሬዝደንት ኤርዶዋን አማካይነት ታኅሣሥ 2/2017 ስምምነት መፈረማቸው አይዘነጋም።
ከሁለቱ አገራት አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ውጥረትን አንግሶ የቆየው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ የተቀሰቀሰው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከፈረመች በኋላ ነበር።
ኤርዶዋን ስምምነቱን "ታሪካዊ" በማለት በሁለቱ አገራት መካከል "ሰላም እና ትብብር ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ" እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸዋል።
በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ "በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ስር አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ዘላቂ የባሕር መተላለፊያ" እንድታገኝ የሚያስችል የንግድ እና የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ በቅርበት ይሠራሉ።
ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አዲስ አበባ ላይ የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ነበር በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ውዝግብ የቀሰቀሰው።
ማኽሮን ቅዳሜ ዕለት በነበራቸው ኦፊሴላዊ ጉብኝት ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ጠቅሰው ሀገራቸው የበኩሏን አስተዋፅዖ እንደምታደርግ አሳውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በበኩላቸው ሁለቱ መሪዎች ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ማኽሮን በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን ፈረንሳይ ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነች ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ እንደሚደግፉ ገልፀው "በሚቀጥሉ ሳምንታት" የዕዳ ሽግሽግ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ማኽሮን "በቀሚጥሉት ጥቂት ሳምንታት የ3 ቢሊዮን ዩሮ ዕዳ ሽግሽጉን ለማጠናቀቅ እንሠራለን" ብለዋል ይላል የሮይተርስ ዘገባ።
ዐቢይ እና ማኽሮን በቅርቡ የታደሰውን ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት ጎብኝተዋል።
በፈረንሳይ መንግሥት የዲቨሎፕመንት ኤጀንሲ 25 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የተገነባው ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት በቅርቡ ለሕዝብ ክፍት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የፈረንሳይ የአርክቴክቸር ባለሙያዎች እና ሌሎች ሙያተኞች በእደሳው ላይ እንደተሳተፉ ማኽሮን ጠቅሰዋል።
ኢማኑኤል ማኽሮን ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ጂቡቲን ከጎበኙ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ይፋዊ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።