ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞ ታጣቂዎች የሚወስዱት "የተሃድሶ ሥልጠና" ምንድን ነው? የቀናት ሥልጠናስ በቂ ነው?
ባለፈው ወር በትግራይ ክልል የተጀመረው የቀድሞ ተዋጊዎች የተሃድሶ ሥልጠና ወደ አፋር ክልል ተሻግሯል።
ለመሆኑ ሥልጠናው ለምን ያክል ጊዜ ይሰጣል? ምን ያክል የቀድሞ ታጣቂዎችስ በዚህ ሥልጠና ተሳታፊ ይሆናሉ? የገንዘብ ድጋፍ ጉዳይስ?
በቀድሞው የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሀጂ ስዩም አወል የሚመሩ እና በክልሉ ነፍጥ አንግበው ሲዋጉ የነበሩ አንድ ሺህ 750 'የአፋር ፌደራላዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ' (የአፋር ፌደራሊስት ኃይሎች) ታጣቂዎች ታኅሳስ 9/2017 ዓ.ም. የተሃድሶ ሥልጠና ጀምረዋል።
ባለፈው ኅዳር ወር መጀመሪያ ከአፋር ክልል መንግሥት ጋር "የሰላም ስምምነት" የፈረሙት ታጣቂዎች አብዓላ ጊዜያዊ ማዕከል መግባታቸውን ብሔራዊ የተሃድሶ ከሚሽን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ መሰለ የቀድሞዎቹ ታጣቂዎች ወደ 'ሲቪሊያን' ሕይወት ሲመለሱ "በቂ ግንዛቤ እና ስነ ልቦና ጥንካሬ" እንዲኖራቸው ይፈለጋል ይላሉ።
ለዚህም የተሃድሶ ኮሚሽን ከጤና ሚኒስቴር እና ሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "የማሰልጠኛ ሰነዶች" ማዘጋጀቱን የጠቀሱት ኃላፊው፤ በዋናነት የቀድሞ ታጣቂዎቹ የሦስት ቀን የስነ ልቦና (ሳይኮ-ሶሻል) እና የሲቪክስ ስልጠና እንደሚወስዱ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
"በአጠቃላይ ከጦርነት ወደ ሰላም ሲሄዱ የተሻለ ሥነ-ልቡና እና አገራዊ [እውቅና] ይዘው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የሚያስችል ሥልጠና ይሰጣቸዋል" ሲሉ ይገልፃሉ።
ለሁለት ቀናት የሚሰጠው የሥነ-ልቡና ሥልጠና ቀዳሚ ክፍል የግጭት እና የጦርነት ጫና ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ የግጭት አስከፊነት የሚያስረዳ ነው ይላሉ።
". . . ጦርነት የሚያሳድረውን ተፅዕኖ እያብራራን ከአዕምሮ ጤና እና ከሥነ-ልቡና ድጋፍ ጋር በማያያዝ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ማኅበራዊ ሕይወት እንዲመጡ የሚያስችል [ሥልጠና] እንሰጣለን። ይህ አንዱ ክፍል ነው።"
የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ደግሞ ሌላኛው ክፍል ሲሆን የቀድሞ ታጣቂዎች ተግባቦት፣ ችግር የመፍታት ችሎታ፣ የውሳኔ አቅም እና የመሳሰሉ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ የሚያግዝ መሆኑን ኃላፊው ይጠቁማሉ።
"ማኅበረሰቡ [የቀድሞ ታጣቂዎችን] እንዴት ይቀበላል? ከቀድሞ ታጣቂዎች ምን ይጠበቃል? ምን አይነት መደጋገፍ እና መስተጋብር ይኖራል? እንዴት ነው ከማኅበረሰቡ ጋር ተሳስሮ ውጤታማ ሕይወትን መምራት የሚቻለው?" የሚሉ ከማኅበረሰቡ ጋር ለመቀላቀል አስፈላጊ የሆኑ የሥነ-ልቡና ዝግጁነት እንዲኖራቸው ማድረግ ደግሞ ሌላኛው ክፍል መሆኑን ያስረዳሉ።
በተሀድሶ ሥልጠናው ለአንድ ቀን የሚሰጠው የሲቪክስ ትምህርት የሰላም ግንባታ እና ትርፍ፣ የሐሳብ ልዩነቶችን በሰላም መፍታት እንዲሁም ትጥቅ መፍታት እና ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል የሚኖረውን ሚና የሚያጠቃልል መሆኑን አቶ ሀብታሙ ይናገራሉ።
"ስለ አገር ግንባታ፣ አገራዊ ማንነት፣ አገራዊ እሴቶች፣ ፌዴራሊዝም እና ዲሞክራሲ፣ ኢትዮጵያ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ. . ." የሲቪክስ ሥልጠናው አባሪ መሆኑንም ይገልፃሉ።
ሥልጠናውን በተደጋጋሚ በሰጡ እና የአሠልጣኞች ሥልጠና በወሰዱ አሠልጣኞች ይሰጣል።
የተሃድሶ ሥልጠናው "ሁለገብ" እንዲሆን በአስተርጓሚዎች እና የቋንቋው ተናጋሪ በሆኑ አሠልጣኞች እንደሚሰጥም ይጠቁማሉ።
"እንዴት አድርገን ማስረዳት እና ግንዛቤ መፍጠር እንችላለን? በየትኛው የተሻለ ሐሳብ መረዳዳት ይቻላል?. . ." የሚለው የተጤነበት ጉዳይ መሆኑን እና ሥልጠናው የቀድሞ ታጣቂዎቹ "በሚፈለጉት መንገድ" እየተሰጠ ነው ብለዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ ወደ መደበኛ ሕይወት ለመመለስ የሦስት ቀን የተሃድሶ ሥልጠና ብቻ ይሰጣቸዋል።
ነፍጥን አማራጭ አድርጎ ለተነሳ ታጣቂ የሦስት ቀን ስልጠና በቂ ነው ወይ? ተብለው የተጠየቁት የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ሀብታሙ "በቂ ነው" ይላሉ።
ለዚህም ሥልጠናው "ደረጃውን የጠበቀ" ነው የሚሉት ኃላፊው፤ "ሙከራ" ተደርጎ የተረጋገጠ ከመሆኑ ባሻገር የቀድሞ ታጣቂዎቹ የፖለቲካ "ንቃተ ኅሊና" ከግምት ውስጥ መግባቱን ተናግረዋል።
የአፋር የቀድሞ ተዋጊዎች የተሃድሶ ሥልጠና ለአንድ ሳምንት የሚዘልቅ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ ሥልጠናውን አጠናቀው ሲወጡ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን በመጀመሪያው ዙር ታጣቂዎችን የማሰባሰብ፣ ትጥቅ የማስፈታት እና ወደ ማኅበረሰቡ የመቀላቀል (ዲዲአር) ውጥኑ 75 ሺህ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ ይሰራል።
በትግራይ ክልል የተጀመረው የመጀመሪያው ዙር የተሃድሶ ሥልጠና እና የማቋቋም ስራ ለአራት ወራት የሚቆይ እንደሆነ አቶ ሀብታሙ መለሰ ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹን ለማቋቋምም ኮሚሽኑ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል። የክልል መንግሥታትም ለቀድሞ ታጣቂዎች በዘላቂነት መቋቋም "ማዕቀፎችን" እንደሚያዘጋጁ ይጠበቃል።
የአፋር ክልል የቀድሞ ታጣቂዎች በሚቀጥለው ሳምንት ሥልጠናቸውን ጨርሰው ወደ ማኅበረሰቡ ከተቀላቀሉ በኋላ ኮሚሽኑ የገንዘብ ድጋፍ እንደማያደርግላቸውም አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል።
የቀድሞ ታጣቂዎቹ አዲሱን ሕይወታቸው ለመጀመር የሚሰጣቸውን የገንዘብ ድጋፍ የመጀመሪያው ዙር ሥልጠና እስኪያበቃ ድረስ መጠበቅ እንደሚኖርባቸው የጠቆሙ ሲሆን፤ ይህንንም "አውቀው እና ተስማምተው" መግባታቸውን ገልጸዋል።
መንግሥት "አፋር ነፃ አውጪ ግንባር" በሚል ከሚጠሩ ታጣቂዎች ጋር "የሰላም ስምምነት" ላይ መድረሱን ከዚህ ቀደም ገልጿል።
የክልሉ መንግሥት "ጥያቄ ሲያቀርብ" ለሌሎች የቀድሞ ታጣቂዎቹ የተሃድሶ ስልጠና እንደሚሰጥ አቶ ሀብታሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።