አሜሪካ በጋዛ እርዳታ ለማድረስ ጊዜያዊ የባሕር በር ልትገነባ ነው ሲሉ ባይደን ተናገሩ

ፍልስጤማዊያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ለፍልስጤማዊያን እርዳታ ለማድረስ ጊዜያዊ የባሕር በር ልትገነባ መሆኑን ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አሳውቀዋል።

ጊዜያዊው ጠረፍ ወደ ፍልስጤማዊያን የሚጓዘውን እርዳታ መጠን ከፍ እንደሚያደርገው የሚናገሩት የአሜሪካ ባለሥልጣናት “በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪናዎች” ይጓዛሉ ብለዋል።

ነገር ግን ጊዜያዊ የባሕር በር ማቋቋም ማለት የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ሥፍራው ይሰማራሉ ማለት አይደለም ሲሉ ባይደን አስረግጠዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በጋዛ ካሉ ነዋሪዎች ሩብ ያክሉ ረሀብ ሊያጠቃቸው ጫፍ ደርሰዋል ይላል።

ፕሬዝደንት ባይደን ሐሙስ ዕለት ለታችኛው እና ላይኛው ምክር ቤት ባሰሙት ንግግር ነው ይህን ያሉት።

ፕሬዝደንቱ እንደሚሉት ጠረፉ በአሜሪካ ጦር ሠራዊት የሚገነባ ሲሆን እርዳታውን ከባሕር አውርዶ የባሕር ዳርቻ ላይ የሚወስድ መንገድ ይመቻቻል።

እርዳታ ወደ መሬት ከወረደ በኋላ ማን ነው የሚጠብቀው ወይስ ዕጣ ፈንታው ምን ይሆናል የሚሉት ወሳኝ ጥያቄቀዎች እስካሁን ምላሽ አላገኙም።

የሚመጡ ግዙፍ መርከቦችን መሸከም የሚችል ነው።

የመጀመሪያው እርዳታ በቆፕሮስ በኩል እንደሚገባ የታወቀ ሲሆን እስራኤል እርዳታው ከመተላለፉ በፊት ፍተሻ ታደርግበታለች።

“ይህ ጠረፍ ወደ ጋዛ በየቀኑ የሚገባውን የእርዳታ መጠን ያሳድገዋል” ብለዋል ፕሬዘደንት ጆ ባይደን።

አክለው እስራኤል ተጨማሪ እርዳታ እንዲገባ በመፍቀድ “የራሷን ድርሻ ልትወጣ” ይገባል ብለው “የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ልትጠብቅ እንደሚገባም” አሳስበዋል።

ባፈለው ጥቅምት ሐማስ ወደ እስራኤል ድንበር ገብቶ ጥቃት ከፈፀመ በኋላ ነው እስራኤል በጋዛ የመሬት ለመሬት ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ የጀመረችው።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር በእስራኤል የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ቁጥር 30 ሺህ 800 ደርሷል ይላል።

በያዝነው ሳምንት የዓለም ጤና ድርጅት በሰሜን ጋዛ ሕፃናት በረሀብ ምክንያት እየሞቱ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ ማሰማቱ ይታወሳል።

በሰሜናዊ ጋዛ እስከ 300 ሺህ የሚሆኑ ፍልስጤማዊያን ያለ ንፁሕ ውሀ እና ያለ ምግብ እየኖሩ እንዳለ እየተዘገበ ነው።

የአሜሪካ መንግሥት ወደ ጋዛ እርዳታ ለማስገባት የተለያዩ አማራጮችን እየተጠቀመ ሲሆን እስራኤል ይህ እንዲሆን የበኩሏ እንድትወጣ ጫና በማሳደር ላይ ይገኛል።

ባለፈው ሳምንት ከ100 በላይ እርዳታ ሊቀበሉ የወጡ ፍልስጤማዊያን መገደላቸው አይዘነጋም። ፍለስጤማዊያኑ እንደሚሉት እርዳታ ለመቀበል ወጥተው ሳለ ነው የእስራኤል ወታደሮች ተኩስ የከፈቱባቸው።