የፊፋ ፕሬዝዳንት ምዕራባውያን በኳታር ላይ የሚሰነዝሩትን ትችት “ግብዝነት” ሲሉ ወቀሱ

በዓለም ዋንጫ ዋዜማ ላይ ምዕራባውያን በኳታር ስላለው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ የሚያወጡት ሪፖርት “ግብዝነት ነው” ሲሉ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ወቀሱ።

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ የበላይ አካል ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ ዶሃ ውስጥ በተካሄደ ልዩ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለአንድ ሰዓት ያህል ባደረጉት ንግግር፣ ኳታርን እና የምታስታናግደውን ውድድር አጥብቀው ተከላክለዋል።

በኳታር ነገ እሁድ ከሚጀመረው የዓለም ዋንጫ ውድድር ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ላይ በስደተኛ ሠራተኞች ሞት እና በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን አያያዝ ዙሪያ ተደጋጋሚ ክሶች ሲቀርቡት ቆይቷል።

ኢንፋንቲኖ በንግግራቸው መክፈቻ ላይ ጠንካራ ቅሬታ እንደሚሰማቸው በመግለጽ፣ “በእርግጥ የኳታር ዜጋ፣ አረብ፣ አፍሪካዊ፣ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ፣ አካል ጉዳተኛ ወይም ስደተኛ ሠራተኛ አይደለሁም። ነገር ግን በውጭ አገር ውስጥ እንደ ውጭ አገር ዜጋ መድልዎ እና መጠቃት ምን ማለት እንደሆነ እነሱ የሚሰማቸውን ስለማውቅ ይሰማኛል” ብለዋል።

የፊፋው ፕሬዝዳንት ኢንፋንቲኖ በንግግራቸው “እኔ አውሮፓዊ ነኝ። ለሌሎች የሞራል ትምህርት ከማስተማራችን በፊት ለ3000 ዓመታት በዓለም ዙሪያ ሲፈጸሙ ለነበሩት ድርጊቶች፣ ለቀጣዮቹ 3000 ዓመታት ይቅርታ መጠየቅ አለብን።

“በእርግጥ አውሮፓ ለእነዚህ ሕዝቦች የወደፊት ዕጣ የምትጨነቅ ከሆነ፣ ኳታር እንዳደረገችው ሕጋዊ መስመሮችን በመክፈት እነዚህ ሠራተኞች ወደ አውሮፓ መጥተው እንዲሠሩ ማድረግ አለባቸው። የተወሰነ ተስፋ እና መልካም ዘመን ፍጠሩ” ብለዋል።

አክለውም “ትችቶቹን ለመረዳት እቸገራለሁ። ለእነዚህ ሰዎች የወደፊት ተስፋ ለመፍጠር በትምህርት ለመርዳት የሚያስችል ገንዘብ ማውጣት አለብን። ሁላችንም እራሳችንን ማስተማር አለብን። ለውጥ እና መሻሻል ጊዜ ይፈልጋል።

“ነገር ግን ይህ የአንድ ወገን የሞራል ትምህርት ግብዝነት ብቻ ነው። ከ2016 (እአአ) አንስቶ ኳታር እያሳየች ያለውን መሻሻል ለምን እውቅና እንደማይሰጠው ጥያቄ ይሆንብኛል።

“ኳታር የዓለም ዋንጫን እንድታስተናግድ ከ12 ዓመት በፊት የተሰጠው ውሳኔ ላይ የሚቀርበውን ትችት መቀበል ቀላል አይደለም። አሁን ኳታር ዝግጁ ናት፣ ይህም እስካሁን ከታዩት የዓለም ዋንጫዎች የላቀው ይሆናል።

“ለኳታር መከራከር የለብኝም፣ እነሱ እራሳቸውን መከላከል ይችላሉ። እኔ የምከራከረው ስለ እግር ኳሱ ነው” ብለዋል።

ኢንፋንቲኖ እንዳሉት ኳታር ከዓለም የሥራ ድርጅት ጋር በመሆን የስደተኛ ሠራተኞችን ሁኔታ የሚከታተል ጽሕፈት ቤት የከፈተች ሲሆን፣ በሥራ ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው ሠራተኞችም “እንደደረሰባቸው ጉዳት መጠን የበርካታ ዓመታት ደሞዛቸውን እና በሕግ ካሳ እንዲያገኙ ይደረጋል” ብለዋል።

ከፍተኛ ትችቶችን ስታስተናግድ የቆየችው አስተናጋጇ ኳታር እሁድ ከሰዓት በኋላ በሚካሄደው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ከኢኳዶር ጋር ትገጥማለች።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ዘጋርዲያን ባወጣው ዘገባ ኳታር የዓለም ዋንጫ የማስተናገድ ዕድልን ካገኘችበት ጊዜ አንስቶ ከሕንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከኔፓል፣ ከባንግላዲሽ እና ከሲሪላንካ የመጡ 6,500 ስደተኛ ሠራተኞች ለሞት ተዳርገዋል።

ይህ አሐዝ መሠረት ያደረገው በኳታር ውስጥ ከሚገኙ የሟቾቹ ሠራተኞች አገራት ኤምባሲዎች የተገኘን መረጃን ነው።

ነገር ግን የኳታር መንግሥት የቀረበው አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር ከዓለም ዋንጫ ዝግጅት ጋር ከተያያዙ ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዙ አይደለም ሲል ተቃውሞውን ገልጿል።