ሩሲያ ጆ ባይደን፣ ሂላሪ ክሊንተንና በሌሎች ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣለች

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና በሌሎች 12 የአስተዳደሩ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሉን አስታወቀ።

በሩሲያ ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን፣ መከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲን እና ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ጄን ሳኪ ይገኙበታል።

አሁን በስልጣን ላይ ከሚገኙት በተጨማሪ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ እና ፕሬዝዳንታዊ እጩ ሂላሪ ክሊንተን እና የጆ ባይደን ልጅ ሃንተር ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

ሩሲያ በግለሰቦቹ ላይ የጣለችው ማዕቀብ ወደ ሞስኮ እንዳይገቡ እና በሩሲያ ያላቸው ንብረት እንዳይንቀሳቀስ የሚያዝ ነው።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማዕቀብ ከተጣለባቸው ግለቦች ጋር ንግግር ማድረግ ከተፈለገ ግን ማዕቀብ መጣሉ እክል አይሆንም ብሏል።

ሩሲያ ጦሯን ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ በርካታ ማዕቀቦች በምዕራባውያን ተጥሎባት ይገኛል።

ምዕራባውያኑ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌይ ላቭሮቭ እና ፕሬስ ሴክሬታሪ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።

አሜሪካ ትናንት ተጨማሪ 11 የሩሲያ የጦር መኮንኖች ላይ ማዕቀብ መጣሏን ይፋ ያደረገች ሲሆን፤ በቤላሩሱ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ላይ ማዕቀብ ልትጥል እንምትችል ዋሽንግተን አመላክታለች።

ቤላሩስ የሩሲያን የዩክሬን ወረራ በመደገፍ ከሞስኮ ጎን ስለመሰለፏ በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።

ዩናይትድ ኪንግደም በበኩሏ ተጨማሪ 370 ሩሲያውያን ላይ ማዕቀብ ጥላለች። ከእነዚህ መካከል የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዝደንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ይገኙበታል።

ሩሲያ በአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሏ የተሰማው ፕሬዝደንት ባይደን በቀጣይ ሳምንት በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ብራሰልስ እንደሚጓዙ በተገለጸበት ወቅት ነው።

በኔቶ አስቸኳይ ስብበሳ ላይ ፕሬዝደንት ባይደን አሜሪካ ለወዳጅ አገራት የተቻላትን ድጋፍ እንደምታደርግ ይገልጻሉ ሲል ዋይት ሃውስ ዘግቧል።