የትግራይ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ውሳኔ ፖለቲካዊ ወይስ ቅያሜ?

ላለፉት አስራ ስድስት ወራት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ በርካቶች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። በሚሊዮኖች የሚገመት ሀብት ንብረት ወድሟል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለምግብ እና ለመድኃኒት እጥረት ተጋልጠዋል።

ጦርነቱ ካስከተለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ጉዳት በተጨማሪ ጥላውን በእምነት ታቋማት ላይ እያሳረፈ ነው። ከጥቂት ሳምንታት በፊት በትግራይ ክልል የሚገኙ የክርስትና እና የአስልምና እምነት መሪዎች በማዕከል ከሚገኙት የየእምነቶቹ ተቋማት ራሳቸውን መነጠላቸውን አሳውቀዋል።

የመለየት ውሳኔ

ከሦስት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባል የሆኑ የትግራይ ጳጳሳት እና ቀሳውስት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር የነበራቸውን አስተዳደራዊ ግንኙነት በማቋረጥ አዲስ ቤተ ክህነት ማቋቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።

ይህንንም ተከትሎ የትግራይ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በበኩሉ ከኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር የነበረው ግንኙነት ማቋረጡን ገልጿል።

የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት የኡለማ ምክር ቤት አባልና የሰላምና የእርቅ ዘርፍ ኃላፊ ሐጂ መሐመድ ሲራጅ ግን "ተለያይተናል" ማለት ተገቢ አለመሆኑን ይናገራሉ።

"የአንድ አገር ሰዎች ነን" ያሉት ኃላፊው፤ "ትግራይ ውስጥ ያጋጠመው ችግር በቀሪው ኢትዮጵያ ያለ ችግር መሆኑን ያውቁታል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በኢትዮጵያ ድህረ ምረቃ ሥነ መለኮት ትምህርት ቤት የሥነ መለኮት መምህር እንዲሁም 'የባለንጀራዬ' እንቅስቃሴ አጋር መስራች ዳይሬክተር ዶክተር ተካልኝ ነጋ፣ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ያለው የአደረጃጀት በክልሎች ደረጃ የተዋቀረ ስለሆነ የትግራይ ምክር ቤት በዚህ መቀጠሉን ነው የሚያሳየው ይላሉ።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲና አወቃቀር ግን በዋነኛነት በክልሎች ደረጃ ነው ማለት እንደማይቻል ያስረዳሉ።

ከዚህ በመነሳትም የሃይማኖት ተቋማቱ እየወሰዱት ያለው እርምጃ "ፖለቲካዊ ጫና እንዳለበት" መናገር እንደሚቻል ያስረዳሉ።

"እንደዚህ አይነት መከፋፈል ሲደረግ በእኔ አመለካከት በተጠሪዎቻቸው አማካይነት ተቀምጠው እርስ በርሳቸው በአንድ ጉዳይ ላይ ልዩነታቸውን በግልጽ ተነጋግረው የተወሰነ ስላልሆነ በጣም ፖለቲካዊ ጫና ያለበት ውሳኔ አድርጌ ነው የምወስደው።"

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማቲያስ መጋቢት ወር 2021 ላይ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ችግሮች እንዳሉ በመግለጽ "ብዙ ጊዜ በተለይ በትግራይ እየተፈጸመ ያለው አረመኔነት እንዲቆም ለመናገር ፈልጌ አልሆነልኝም። ፈቃድ አልተሰጠኝም" ብለው ነበር።

ይህ መልዕክት በአሜሪካ ቅዱስ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ በሚሰሩት ፕሮፌሰር ዴኒስ ዋድሌይ የተቀዳ ሲሆን "በቤተክርስቲያን እና በደብረ ዳሞ ገዳም ላይ መድፍ ተተኩሷል፣ መነኮሳት እና የሚኖሩበት ፈርሷል፣ የሃይማኖት አባቶች ተገድለዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ ውጪ ቅዱስ ሲኖዶሱ ይሁን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጦርነቱ ያስከተለው ሰብዓዊ ኪሳራ፣ በሃይማኖት ተቋማት እና ምእመኑ ላይ የደረሰው ጉዳት የሚመለከት የሰጠው አስተያየት የለም።

ቢቢሲም የትግራይ ሃይማኖት አባቶች ውሳኔን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም ለጊዜው አልተሳካለትም።

ቅሬታ

በትግራይ የሚገኙ የእስልምና እና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለመለያየታቸው እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት በፌደራል ስር የሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት በትግራይ ሕዝብ እና የእምነት ቦታዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ አላወገዙም የሚል ነው።

የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝደንት ሼኽ አደም ዓብደልቃድር ለአሜሪካ ድምጽ በሰጡት ቃል በጦርነቱ ወቅት "ሰላማዊ ሙስሊሞች፣ ኢማሞች እና ኡላማዎች ተገድለዋል" ብለዋል።

"የሃይማኖት አባቶች ጦርነት ላይ መሳርያ ይዘው አይዋጉም። ሆኖም ብዙ ቁጥር ያለው ሙስሊም ተገድሏል። የአልነጃሺ መስጂድም ሆነ ተብሎ ጉዳት ደርሶበታል። ይህ ሁሉ ችግር ሲደርስ ይታወቃል፤ ችግራችንን ነግረናቸዋል። ሆኖም አልተረዱንም" ብለዋል።

በዚህ ምክንያትም ከፌደራል የእስልምና ጉዳዮች ምክርቤት ጋር የነበራቸው ግንኙነት መቋረጡን አስታውቀዋል።

ሐጂ መሐመድ ሲራጅ በበኩላቸው በጦርነቱ ምክንያት በአፋርና ሰሜን ወሎ ከ110 በላይ መስጊዶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ያስታውሳሉ።

"ይህ ችግር ሁሉም ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው። ብዙ የሃይማኖት አባቶች፣ ቁርአን አስተማሪዎች ሞተዋል። ይሄን አደረገው የምንለው የርስ በርስ ግጭታችን ነው። እኛ ከዚህ ያለውም ሆነ ከዚያ ያለውን ጦረኛ አንደግፍም፤ ለምን ደም ይፈስሳል፣ ንብረት ይፈርሳል፣ የሃይማኖት ተቋማት ይፈርሳሉ እያልን እኮ እንናገራለን" ብለዋል።

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚኖረው የእምነቱ ተከታይ ከማል መሐመድ ያሲን ምክር ቤቱ የወሰደው እርምጃ "ጫና የለውም ለማለት ባያስደፍርም ትክክለኛ ነው" ብሎ እንደሚያምን ይናገራል።

"በጦርነቱ ምክንያት ክልሉ ላይ የደረሰው ጉዳት ለማወቅ ሪፖርቶች ማንበብ በቂ ነው። ይሄንን አይተውም ሆነ ስናወራው የነበረው ጥሪ ተቀብለው ግን በደል ደርሶባቸው ይሆን? ብለው አላዩንም" የሚል ቅሬታ እንዳለውም ይገልጻል።

ሐጂ መሐመድ ሲራጅ ግን በተደጋጋሚ ጦርነት አያስፈልግም ብለው መናገራቸውን ይገልጻሉ።

". . . ድርጊቱን እንደ ሃይማኖት አባት መቋወም እንጂ አኩራፊ ሆኖ መናገር አይታየኝም። እንደ ተቋምም ሊባል አይገባም። ከዚህም ከዚያም ያሉት የሃይማኖት አባቶች ጉዳዩ ከመፈጸሙ በፊት ጦርነት አያስፈልግም፣ ሁሉም ተጎጂ ነው፣ ንብረት ያፈርሳል፣ ህይወት ያጠፋል ስንት ጊዜ ነው የተባለው? ከዚህ ገለልተኛ ሆነው ነው መናገር ያለባቸው። ለምን እንደዚህ እንዳሉ አናውቅም" ብለዋል።

ዶክተር ተካልኝ በበኩላቸው በእምነት ቤተሰቦች የሆኑ እና ወንድማማቾች ነን ብለው የሚያምኑ እነዚህ አካላት የፈጠሩት አዲስ የእምነት አንቀጽ [አርቲክል ኦፍ ፌይዝ] እንደሌለ በመጥቅ የእነዚህ ውሳኔዎች አንድምታ ቅያሜ መሆኑን ያነሳሉ።

"ችግሩ በምናልፍበት ጊዜ አብራችሁን ልትቆሙ ሲገባ ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነው ሂደት እኛ ላይ ጉዳት እያደረሰ ካለው አካል ጋር ተባብራችኋል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ቅያሜ አለን የሚል አይነት ነው ብዬ አየዋለሁ። ክርስትና ውስጥ በደል ሲደርስ፣ እምነት ወደ ጎን ሲደረግ ቤተ ክርስቲያን ድምጽ መሆን አለባት የሚል አለ። ከዚህ የተነሳ ያላቸው ቅያሜ የገለጹበት ነው ብዬ አስባለሁ" ይላሉ።

ፖለቲካ እና ሃይማኖት

የ'Understanding Religion and Society in Ethiopia' ፀሐፊ እና በሮሃምፕተን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነው መሐመድ ግርማ በኅዳር ወር 2021 ላይ 'ሃይማኖት በአንድ ወቅት ኢትዮጵያን አድኗታል፤ አሁንስ አገሪቷን ከመፍረስ ለመታደግ ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል?' በሚል ርዕስ በጻፈው ጽሁፍ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ የሃይማኖት ተቋማት ከደረሰባቸው ሞራላዊ ውድቀት የሚመነጭ ነው ይላል።

ይህ በበርክሌይስ የሃይማኖት፣ ሰላም እና ዓለማዊ ግንኙነቶች ማዕከል የታተመው ጽሁፍ "የሃይማኖት ቡድኖቹ የሰላም እና እርቅ፣ አብሮ የመኖር ምንጭ መሆን ስላልቻሉ በሕብረተሰብ ውስጥ ለሚታየው የሞራል ኮምፓስ መጥፋት ተጠያቂ ናቸው" ሲል ይወቅሳል።

ለዚህም የቤተክርስቲያኒቷ ፓትሪያርክ መንግሥት በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለው ሲናገሩ ሌሎች ካህናት ደግሞ መንግሥት መደገፋቸውን ጠቅሷል።

ይህ "የእምነት ተቋማት በውስጣቸው ከብሔር ጋር የሚያያዝ ቀውስ እንዳለባቸው የሚያመላክት ነው" ሲል ይገልጸዋል።

ዶክተር ተካልኝ ነጋ በበኩላቸው "አሁን ሁላችንም ህመም ውስጥ ያለንበት ጊዜ ነው፤ በዚህ ጊዜ ሁላችንም እንዲሰማ የምንፈልገው ድምጽ የእኔ ብቻ የሚለው ነው፤ መወቃቀሱ ተፈጥሯዊ ቢሆንም ሰው ማድመጥ የሚፈልገው የራሱን ብቻ ነው" በማለት የትግራይ የሃይማኖት ተቋማት ያሳዩት ልዩነት ሃይማኖታዊ ነው ለማለት እንደሚከብድ ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ የትምህርት እና ስልጠና ሃላፊ የነበሩ አሁን በሜልበርን አውስትራሊያ የቅድስት ማርያም ደብረጽዮን ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት አባ ሰረቀ-ብርሃን ወልደሳሙኤል የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ እንዳይኖር "ክህደት" ተፈጽሞበታል በማለት ለውሳኔው መነሻ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ ነው ይላሉ።

"በጎቼን ጠብቅልኝ ተብሎ ሃላፊነት የተሰጠው መሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ትግራይ ላይ ሲፈጸም የነበረው ማውገዝ እና መቃወም ነበረበት። ይህን ባለማድረጉ ግን ህዝብ አዝኗል፣ ካህናትም አዝነናል" ይላሉ።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች የኡላማ ምክር ቤት አባል እና የሰላም እና እርቅ ዘርፍ ኃላፊው ሐጂ መሐመድ በበኩላቸው "እኔ እንደ አንድ የሃይማኖት መሪ የሰው ህይወት የሚቀጥፍ፣ የሰው ንብረት የሚያጠፋ፣ ሰው ከቦታ የሚያፈናቅል ሥራ ትክክል አይደለም ማለት አለብን። የተወገዘ ነው" ይላሉ።

የእስልምና እምነት ተከታዩ ከማል በበኩሉ የትግራይ የእሰልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሆነ የኢትዮጵያ በፖለቲካ ጫና ምክንያት ብዙ ስህተቶች ስለተሰሩ "የፖለቲካ መሳሪያ ሆኗል" የሚል ቅሬታ ሲቀርብበት እንደነበረ ይገልጻል።

ሆኖም በእስልምና ሃይማኖት ግፍና በደል ሲደርስ ከአማኙ ይሁን ከተቋሙ የሚጠበቁ ሦስት ነገሮች አሉ ይላል።

እነዚህም "ከተበዳይ ጋር መቆም፣ የሚፈጸመው በደል ማጋለጥ፣ ካልተቻለ ደግሞ የሚፈጸሙ ነገር መጸየፍ ነው። በፌደራል ስር የሚገኙ መሪዎቻችን ግን ከዚህ ተጻራሪ ጎን ነው የቆሙት" የሚል ስሜት እንዳለው ተናግሯል።

"ከዚህም ከዚያም የሚጠፉት ወገኖቻችን ናቸው።. . .ከትንሽ ጊዜ በኋላ ግን የዘረኝነት ስሜት እየተንጸባረቀ፣ እየተስፋፋ ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን፣ አባቶቻችን እናቶቻችን እያጣን ነው። ከሁሉም አቅጣጫ ሰው እየሞተ ነው፤ ለምን ይሞታል ማለት ነው የሚገባን" ሲሉ የሚሞግቱት ደግሞ ሐጂ መሐመድ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪዎች በተቀያየሩ ቁጥር መሞት፣ መፈናቀል፣ የለበትም የሚሉት ሐጂ መሐመድ "አፋር ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ ሌላ ላይ የሚፈናቀሉትና የሚሰቃዩት ወንድሞቻችን ሕዝቦቻችን ናቸው ብለን ነው የምናምነው። ይህን ማውገዝ ነው የሚጠበቅብን" ብለዋል።

ጥፋት ሲኖር በሃይማኖት ቤተሰቦች መካከል የደረሰሰን በደል አላወገዙም፣ የሚያስፈልገንን ድጋፍ አላደረጉልንም ብሎ መወቃቀስ ያለ ነው የሚሉት ዶክተር ተካልኝ፤ "ችግሮቻቸው ላይ ለመነጋገር አንድ መድረክ ሳይፈጥሩ የብቻ ውሳኔ መወሰናቸው ግን ሃይማኖታዊ አሰራር አይደለም" ሲሉ ይወቅሳሉ።

"እየተወቀሰ ያለው አካል ለምን የሚጠበቀውን ምላሽ አልሰጠም የሚለው አልተሰማም። ጥፋቱ ከሁሉም አቅጣጫ [ከፌደራል እና ከክልል] እንዳለ እንሰማለን። እንዲህ አይነት መወቃቀስ ግን ጥፋቱ የሁሉም ነው የሚል መልዕክት አያስተላልፍም። ለመወቃቀስ፣ ንግግር ለመጀመር መነሻ የሚሆን እንጂ ፍቺ ለመጀመር የሚያስችል ሁኔታ ላይ ነን ብዬም አላምንም" ሲሉ ያክላሉ።

መጪ ስጋቶች

አቶ ግርማ መሐመድ በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ለውጥ መምጣት እንዳለበት በመግለጽ በመካከላቸው አንድነት ለማምጣት እና ከፖለቲካዊ ጫና ነጻ የሚሆኑበት ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት ያምናሉ።

አሁን በክልሉ እና በፌደራል ስር በሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት መካከል እየተፈጠረ ያለውን ልዩነት ለመፍታት መጀመርያ ፖለቲካዊ እርጋታ መምጣት እንዳለበት የሚገልፁት ዶክተር ተካልኝ፤ "መጪው ፖለቲካ ሰላም፣ መተማመን እና አብሮ መኖርን የሚፈጥር ከሆነ ተለያይተናል ያሉትን ማስታረቅ አይከብድም" ሲሉ ይናገራሉ።

"ፖለቲካው ከተስተካከለ የሃይማኖት ተቋማት እርስ በርሳቸው ተላቅሰው፣ አጥፍተናል በድለናል የማለት፣ ሌላው እግር ስር ወድቀው ይቅርታ መጠየቅ ስለሚችሉ አብሮ ይስተካከላል ብዬ አስባለው" ሲሉ ተስፋቸውን ገልፀዋል።