ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሲኖዶስ፡ 'የፓትሪያርኩ መግለጫ የግላቸው እንጂ የሲኖዶሱ አቋም አይደለም'
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ከሰሞኑ የሰጡት መግለጫ የግላቸው እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስ ወይም የቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ አይደለም ተባለ።
የፓትሪያርኩ መግለጫ የቅዱስ ሲኖዶሱን አሠራር ያልተከለተለ እና ከሲኖዶሱ ዕውቅና ውጭ የተካሄደ መሆኑን የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊና እና ሲዳማና የጌዲዮ ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ገልጸዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ስለትግራይ እንዳልናገር "ድምጼ ታፍኗል" ማለታቸው ይታወሳል። ፓትርያርኩ በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ግጭት "የአረመኔነት ሥራ" በማለት ጠርተው፤ ዓለም አቀፍ መንግሥታት የንፁኀን ግድያ የሚቆምበትን መንገድ እንዲፈልጉ ሲሉ ተማጽኖአቸውን አቅርበዋል።
ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ በበኩላቸው መሰል መግለጫዎች የሚሰጡት የምዕላተ ጉባኤውን እና የቋሚ ሲኖዶሱን አዎንታ ሲያገኙ መሆኑን አስታውሰው፤ "ቅዱስ ሲኖዶስ እና ቋሚ ሲኖዶስ ሳይወስን ቅዱስ ፓትሪያርኩ በግላቸው ቤተክርስቲያን እና ቅዱስ ሲኖዶስን ወክለው መግለጫ መስጠት አይችሉም" ብለዋል።
በዚህም ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ከሰሞኑ የሰጡት መግለጫ "በግላቸው የሰጡት እንጂ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አይደለም" ሲሉ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያም በቀጣዩ ርክበካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ በአጀንዳ የሚነጋገርበት መሆኑንም ጭምር አስረድተዋል።
"ቅዱስ ፓትሪያርኩ የሰጡት መግለጫ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ያለመሆኑን እየገለጽን ይህንንም የዓለም መንግሥታት በሃገር ውስጥ እና በውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ሊያውቁት እና ሊገነዘቡት ይገባል" ብለዋል።
ይህ በእንዲህ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጌታ ፓሲ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስን በመኖሪያ ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
አምባሳደሯ እና ፓርትሪያርኩ በኢትዮጵያ ስላለው ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ ቀውስ እንዲሁም ፓትሪያርኩ ስላስተላለፉት መልዕክት ተወያይተዋል ሲል የአሜሪካ ኤምባሲ በፌስቡክ ጽፏል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ማን ናቸው?
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስትያን ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆነው የተመረጡት የካቲት 24 2015 ዓ.ም ነበር።
ሊቀ-ጳጳስ አባ ማትያስ "ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ፓትርያርክ ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ-ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ-ተክለ-ኃይማኖት'' ተብለው በቅዱስ ሲኖዶሱ አባላት ሊቃነ-ጳጳሳት 6ኛ ፓትርያርክ በመሆን በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲመተ-ፕትርክናቸውን ተከናውኗል።
አባ ማቲያስ የተወለዱት በትግራይ ክልል በቀድሞ ስሙ ሱብሃና ሳዕስዕ ወረዳ በ1934 ዓ.ም ነው።በተወለዱበት አካባቢ ድቁናን ከአጎታቸው እንደተማሩ ይናገራሉ።
ከዚህ በኋላ ትምህርት ፍለጋ ከሌሎች እኩዮቻቸው ጋር በመሆን ወደ ተንቤን በመሄድ ገዳም ገብተዋል። በተንቤን ገዳማት የሚያስፈልጋቸውን ትምህርት ከተማሩ በኋላ ወደ አክሱም ጽየን በመሄድ ትምህርታቸውን ቀጥለዋል።
ቀጥሎም ወደ ጎንደር በመሻገር ሐዲሳትን ተምረው መምህር ተብለዋል።
አቡነ ማቲያስ ድቁና የተቀበሉት የኤርትራ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ነው። ክህነትን ደግሞ ከብፁዕ አቡነ ዮሐንስ መቀበላቸውን ይናገራሉ።
በቅስና ቄሰ ገበዝ፣ መጋቢ በመሆን ገዳማትን ያገለገሉት አባ ማትያስ፤ ከዚያ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ማገልገል ጀምረዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፓትርያርክ ሆነው ሲመረጡ እርሳቸው አቡነ ቀሲስ ሆነው በመሾም ረዳት ፀኃፊ ሆነው በቤተክህነቱ ማገልገላቸውን ይናገራሉ።
በዚሁ ወቅት በሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ስልጣናት በመሆን ገዳሙን እንዲያስተዳድሩ ቢመረጡም እርሳቸው ግን የቤተክህነት ኃላፊነታቸውን መርጠው ለሶስት ዓመት ያህል አቡነ ተክለሃይማኖትን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
በ1971 ዓ.ም የጳጳሳት ምርጫ ሲደረግ ተመርጠው ኤፊስ ቆጶስ በመሆን ተሹመው ወደ እየሩሳሌም ሊቀጳጳስ ሆነው ሄደዋል።
በእየሩሳሌም ሳሉ ወታደራዊው መንግሥት ደርግ በኃይማኖቶች ላይ ያለውን አሉታዊ አቋም በመቃወም ካወገዙ በኋላ ወደ አሜሪካ አቅንተዋል።
ደርግ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ ብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት መጥተዋል።
በኋላም ሲኖዶሱ በአሜሪካ ያላቸውን ጵጵስና አጽድቆ በአሜሪካ የሚኖሩ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማኞችን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ከዚያ በኋላ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ሞትን ተከትሎ ሊቀ-ጳጳስ አባ ማትያስ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ ፓትርያርክ ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ-ጳጳስ ዘአክሱም፣ ወዕጨጌ ዘመንበረ-ተክለ-ኃይማኖት ተብለው ተሾመዋል።