ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሙስሊም ማህብረሰብን ይቅርታ ጠየቁ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ፣ አዳነች አቤቤ ትናንት እሁድ "ለተፈጠረው ነገር በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ" አሉ።
ምክትል ከንቲባዋ ትናንት በመስቀል አደባባይ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የአፍጥር ስነ ስርአት መስተጓጎሉን አስታውሰው፤ ይህ የሆነው "ወቅታዊ የደህንነት እና የጸጥታ ሁኔታን ከግምት በማስገባት የቦታው ስፋት እና ርዝመት ውስን እንዲሆን ባቀረብነው ሀሳብ አዘጋጅ ኮሚቴው ባለማመኑ ብቻ መሆኑ ግልጽ እንዲሆን እንፈልጋለን" ብለዋል።
ምክትል ከንቲባዋ የትናንት እሁድ፣ ምሽት ሁኔታ የሁላችንም ሰላም እና ደህንነት እንዲጠበቅ አስፈላጊ ጥንቃቄ ለማድረግ የጸጥታ አካላት ጥበቃ ለማድረግ ብቻ የተንቀሳቀሱት እንጂ "በፍፁም የአፍጥር ክልከላ አይደለም" ሲሉ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ለማድረግ ያሰቡ ሙስሊሞች ፍቃድ አልተሰጠም በሚል ምክንያት ወደ መስቀል አደባባይ እንዳይሄዱ ተከልክለው ነበር። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ላይ እንደታየው ፖሊስ የተሰበሰበውን ሕዝብ ለመበተን አስለቃሽ ጪስ ተጠቅሟል።
ምክትል ከንቲባዋ ክስተቱን "አንዳንድ ሃላፊነት የማይሰማቸው አካላት ይህን ጉዳይ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ በማህበራዊ ሚዲያ ሊያራግቡት ሞክረዋል። በዚህ ሁኔታ ላይ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የተሰማውን ቅሬታ የገለጸበት መንገድ ጨዋነት የተሞላበት እና ሰላማዊ መሆኑ ሊደነቅ ይገባል።" ብለዋል።
ስለጉዳዩ እስካሁን የምናውቀው
ትናንት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሙስሊሙ ማህብረሰብ በመስቀል አደባባይ ሊያደርገው የነበረው የአፍጥር ስነ-ስርዓት በመከልከሉ ተቃውሞውን ሲገልጽ ተስምቷል።
በወቅቱ ከተሰሙት መፈክሮች መካከል "በአገራችን ሁለተኛ ዜጋ መሆን የለብንም"፣ "አደባባዩ የእኛም ነው" እና "ለጿሚ አስለቃሽ ጪስ ኢ-ፍትሃዊ ነው" የሚሉ የተቃውሞ ድምጾች ተስተጋብተዋል።
ባለፉት ቀናት በመስቀል አደባባይ ኢፍጣር የማድረግ እቅድ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ዋነኛ መነጋጋሪያ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል።
ሃላል ፕሮሞሽን የተባለ ድርጅት፤ "ታላቅ የጎዳና ላይ ኢፍጣር በኢትዮጵያ" በሚል ከአምስት ሺህ በላይ ሕዝብ የሚታደምበት የኢፍጣር ዝግጅት በመስቀል አደባባይ ለማካሄድ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጾ ነበር።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢፍጣር ስነ-ስርዓቱ በመስቀል አደባባይ ሳይሆን በአዲስ አበባ ስታዲየም መከበር አለበት የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ግንቦት 28 2013 ዓ.ም ጽፋለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ የመስቀል አደባባይ ከመመረቁ በፊት ለሌላ አገልግሎት እንዳይውል የተገለጸ ስለሆነ ፈቃድ ጠያቂዎቹ በሚያቀርቡት ተለዋጭ ቦታ ብቻ እንዲካሄድ ይፈቀድላቸው ብሎ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ግንቦት 28 2013 ዓ.ም ደብዳቤ ጽፏል።
የኢፍጣር ስነ-ስርዓቱን ሲያዘጋጅ የነበረው ድርጅት እንደሚለው ከሆነ የመንግሥት አካል የዝግጅት ቦታውን እንዲቀየር ጠይቋል። ድርጅቱ ግን የዝግጅት ቦታ መቀየሩ አግባብ አይደለም በሚል የኢፍጣር ፕሮግራሙን ለመሰረዝ ተገድጃለሁ ሲል በጻፈው ደብዳቤ አስታውቋል።
በሌላ በኩል ትናንት ምሽት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የጎዳና ላይ የኢፍጣር መርሃ ግብሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ ብሏል።
የከተማ አስተዳደሩ፤ የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ የአደባባዩ የመጨረሻ የግንባታ ሥራዎች አለመጠናቀቃቸው እንዲሁም የቦታው ስፋት እና ርዝመት ከታሰበው ታዳሚ አንጻር እንቅፋት እንዳይፈጥር በውስን አካባቢ እንዲካሄድ እንደ መፍትሔ ተውስዶ ነበር ብሏል።
አስተዳደሩ አዘጋጆቹ ፕሮግራሙን የመሰረዝ አማራጭን ወስደዋል ብሏል የከተማ አስተዳደሩ።
የከተማ አስተዳደሩ ጨምሮም ይህን ለሌላ አላማቸው ለማዋል በማህበራዊ ሚዲያ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዲራገብ ያደረጉ አካላት እንዳሉ አስተውለናል ብሏል።
በዘንድሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በጎዳና ላይ የሚደረጉ የኢፍጣር ስነ-ስርዓቶች በተለያዩ ቦታዎች ተካሂደዋል። በአዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ባህር ዳር፣ ከሚሴ መስል መርሃ ግብሮች ከተካሄዱባቸው ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።