አውሮፓውያን መሪዎች ዜሌንስኪን ለማግኘት አደገኛ በተባለ የባቡር ጉዞ ኪዬቭ ገቡ

ዩክሬን፤ ዜሌንስኪን ለማግኘት ሲሉ ራሳቸውን አደጋ ላይ ጥለው ከፓላንድ ከኪይቭ በባቡር የገቡትን ሦስት የአውሮፓ መሪዎች አወድሳለች።

የፖላንድ፣ ስሎቬኒያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ናቸው ዜሌንስኪን ለማግኘት ሲሉ ማክሰኞ ምሽት በባቡር የዩክሬን ዋን ከተማ የገቡት።

የቼኩ መሪ ዩክሬናዊያን "ብቻችሁን አይደላችሁም" ሲሉ የብርታት ቃል ለግሰዋል።

ሶስቱ ግለሰቦች ከሩሲያ ወረራ በኋላ ዩክሬንን የጎበኙ የመጀመሪያዎቹ ምዕራባዊያን መሪዎች ናቸው።

"ለእኛም ሕይወት እንደምትፋለሙ እናውቃለን። ብቻችሁን አይደላችሁም፤ ከጎናችሁ ነን" ሲሉ የቼኩ መሪ በትዊተር ገፃቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የፖላንዱ ማቴውሽ ሞራዊክ በበኩላቸው አውሮፓ ዩክሬንን ካጣች እንደቀድሞው አትሆንም ብለዋል።

የዩክሬኑ መሪ "ጉብኝታችሁ ለዩክሬን ትልቅ ድጋፍ ነው" ሲሉ ተናግረዋል መባሉ ተዘግቧል።

የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽሚሃል "ሩሲያ ላይ ሊደረግ ስለሚገባው ማዕቀብና ሩሲያ የሽብርተኝነት ደጋፊ ስለመሆኗ ተነጋግረናል" ሲሉ የትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ፅፈዋል።

መሪዎች ውይይት በሚያደርጉበት ወቅት ከጀርባቸው ከባድ ፍንታ በተደጋጋሚ ይሰማ ነበር።

የአውሮፓ ሕብረት እንዳለው ሦስቱ መሪዎች ምንም የተለየ አጀንዳ ይዘው ባይሄዱም ሕብረቱ ግን ስለጉዞው ዕውቀት ነበረው።

የፓላንድ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርሲን ጉዞው አደገኛ እንደነበር አልካዱም። "ነገር ግን ለዓላማ የሚደረግ ነበር" ብለዋል።

ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መሪዎቹ ወደ ኪዬቭ እንደሚጓዙ ለሩሲያዊያን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።

ሦስቱ መሪዎች በባቡር መጓዝ የመረጡት የፓላንድን አየር ኃይል ጄት ከተጠቀሙ ሩሲያ ድርጊቱን እንደ ጠብ አጫሪነት ልታየው ትችላለች ብለው በመስጋት ነው።

ባቡሩ ተመልሶ ወደ ፖላንድ ዋና ከተማ ዋርሶ መች እንደሚመጣ የታወቀ ነገር የለም።

የዩክሬን መሪ በተደጋጋሚ ኔቶ የአገራቸው ሰማይ ላይ በረራ እንዳይካሄድ እንዲያግድ ቢማጸኑም ኔቶ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሏል።

"ለዘመናት ኔቶን ለመቀላቀል በሩ ክፍት ነው ስንባል ነበር። ነገር ግን መቀላቀል እንደማንችል ደግሞ ተነግሮናል። ይህ እውነታው ነው። ሕዝቤ ይህን ተረድቶ ለራሱ መቆም የወዳጆቹን እርዳታ መሻት መጀመሩ አስደስቶኛል" ብለዋል።

ማክሰኞ ዕለት ሩሲያ ኪዬቭ ላይ በከፈተችው ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

የከተማዋ ከንቲባ ቪታሊ ክሊችኮ ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 1 ሰዓት የሚቆይ ሰዓት እላፊ አውጀዋል።