ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሦስት መንገዶችን በመከተል በምትሰራቸው ሥዕሎቿ እውቅናን ያተረፈችው ወጣት
ሐዊ ከባ ከመደበኛ ሥራዋ በተጨማሪ የተለያዩ ጥበቦችን ተጠቅማ በምትሰራቸው የሥዕል ሥራዎቿ ትታወቃለች።
የሥዕል ሥራዎቿን ለመሥራት በዋናነት ሦስት መንገዶችን ትጠቀማለች።
በበርካቶች ዘንድ በይበልጥ የተወደደላት ግን እንጨት በማቃጠል የምትሰራው ሥራ ነው።
ሐዊ ያላትን ትርፍ ጊዜ ተጠቅማ የምትሰራቸውን ሥዕሎች በፌስቡክ ገጿ ላይ በማስተዋወቅ በአገር ውስጥ እና በባህር ማዶ ተወዳጅነትን አትርፋለች።
በነቀምቴ ከተማ ተወልዳ ያደገችው ሐዊ ከባ፣ ከአምቦ ዩኒቨርስቲ በ2011ዓ.ም በኮምፒውተር ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች።
ሐዊ ዩኒቨርሲቲ ከመግባቷ በፊት ሥዕሎቿን ትሰራ የነበረው ክር ወይም ጅማት ተጠቅማ ነበር። ዩኒቨርስቲ ከገባች በኋላ ግን ተጨማሪ ስልቶችን በማዳበር በዓይነት ልዩ አድርጋ መስራት እንደጀመረች ትናገራለች።
"የጥበብ ሥራ ከጀመርኩ ጥቂት ቆየት ብሏል" የምትለው ሐዊ፣ በአምቦ ዩኒቨርስቲ ቆይታዋ ለጥበብ ሥራዎቿ የተለየ ትኩረት የሰጠችበት ጊዜ እንደሆነ ትናገራለች። የጀመረችውም ትናንሽ ነገሮችን በመስራት ነበር።
ሐዊ ሥዕሎቿን ለመስራት የምትከተላቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው ?
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ አንድ የግል ኩባንያ ውስጥ በቋሚነት ተቀጥራ የምትሰራው ሐዊ፣ የሥዕል ስራዋን ብዙ ጊዜ ማታ ማታ እንደምትሰራ ትገልጻለች።
"ሁለት ሥራ መስራት ይከብዳል፤ ነገር ግን ቀን ቀን ትኩረቴን በመደበኛ ሥራዬ ላይ አድርጌ፣ ጥበቡን ስለምወደው ደግሞ ማታ ማታ እሰራለሁ። ድካም ለጥበብ ያለኝን ፍቅር አላሸነፈውም" ትላለች።
በአሁኑ ወቅትም የሥዕል ሥራወቿን በሦስት የተለያዩ መንገዶች በመሳል ለገበያ ታቀርባለች።
ሦስቱ የሥዕል አሰራር መንገዶቿ ውድ በርኒንግ አርት [wood burning art]፣ ስትሪንግ አርት [string art] እና ስኮች ቴፕ አርት [scotch tape art ] ይባላሉ።
ውድ በርኒንግ አርት ማሽን በመጠቀምና እንጨት በማቃጠል የሚሰራ ሲሆን ስትሪን አርት ደግሞ የሚፈለገውን የሥዕል ቅርጽ በምስማር በማዋቀር በዚያ ላይ ጅማት ወይም ክር በመጥለፍ የሚሰራ ነው።
ሐዊ የሥዕል ሥራዎቿን ለመሥራት የምትጠበብበት ሌላኛው መንገድ ስኮች ቴፕ አርት ደግሞ ፕላስተርን በመጠቀም የሰዎችንና የሌሎች ነገሮችን ምሥል በመቅረጽ የሚሰራ ነው።
ሱቢ አርት
ሐዊ ከባ የጥበብ ሥራዎቿን ሱቢ አርትስ በማለት በሰየመችው የፌስቡክ ገጿ ላይ በማስተዋወቅ ብዙ ተከታዮችን አፍርታለች።
ይህንን የጀመረችው ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት መሆኑን የምትናገረዋ ሐዊ፣ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ማስተዋወቋ ገበያ እየሳበላት እንደሆነ ትናገራለች።
"የምሰራቸው የሥዕል ሥራዎች በፌስቡክ ገጹ ላይ በማስተዋወቅ ነበር የጀመርኩት። አሁን ከቀድሞው ይልቅ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል" ትላለች።
'ውድ በርኒንግ' የሚባለው የሥዕል ዓይነት የበለጠ ተቀባይነትን እያገኘላት መሆኑን የምትናገረው ሐዊ ከባ፣ ይህ የጥበብ ዓይነት በኢትዮጵያ እምብዛም የተለመደ አለመሆኑን ትገልጻለች።
"[ማሽኑ]በሚሞቅበት ጊዜ እጅን ይፋጃል፤ ይህ በተወሰነ መልኩ እጄን የሚጎዳ ቢሆንም ለጥበቡ ካለኝ ፍቅር የተነሳ የዚህን ዓይነት የሥዕል ዘዴ ከመሥራት አላገደኝም።" ትላለች።
ሐዊ ከባ ይህንን የሥዕል ሥራዋን ትልቅ ደረጃ የማድረስ ዓላማ እንዳላት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሐዊ እርሷን የሚመጥን ፣ ትውልድን የሚወክል ሥራ የመሥራት ህልም አላት።
የወደፊት እቅዷም ጥበብን የሙሉ ጊዜ ሥራዋ በማድረግ መስራት ነው። "ወደ ሙሉ ሥራዬ በመመለስ፣ የራሴን የሥዕል ማሳያ ስፍራ [ጋለሪ] ኖሮኝ መልካም የሆነ ነገር ለመስራት አስባለሁ" ብላለች ሐዊ።