የግድግዳ ላይ ሥዕል ጥበብ ባለሙያው የኤሌክትሪክ መሃንዲስ ያሬድ ቦጋለ

ያሬድ ቦጋለ ይባላል። የኤሌክትሪካል ምህንድስና ባለሙያ ነው። እጁን በሥዕል ማፍታታት የጀመረው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከገባ ወዲህ ነው። በአሁን ጊዜ ደግሞ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ መሰማራቱን ይናገራል።

ያሬድ ቦጋለ ተምሮ ከተመረቀባቸው የምህንድስና እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያነቱ ወጣ በማለት የተለያዩ የግድግዳ ማስዋቢያ ሥዕሎችን ይሰራል።

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለማችን ላይ እንደተከሰተ ፍራቻም ድንጋጤም ስለነበር ከቤቱ እምብዛም አይወጣም ነበር።

በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ራሱን ቆልፎ የነበረው ያሬድ፣ ጊዜ ማሳለፊያ ይሆነው ዘንድ ብሩሽ እና ቀለምን አነሳ።

አሁን የቤቱን ግድግዳ ዓይን የሚያርፍበት ክፍት ቦታ እስከማይገኝ ድረስ እንዳስዋበው ይናገራል።

ሊቨርፑልና ያሬድ

ያሬድ ግድግዳን የፈጠራ ወረቀቱ ያደረገው ለመጀመሪያ ጊዜ 9 ዓመቱ እያለ መሆኑን ያስታውሳል።

ያኔ በዘጠኝ ዓመቱ ስለ እንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ዝርዝር እውቀት ሳይኖረው ለሊቨርፑል እግር ኳስ ቡድን ጥልቅ ፍቅር ነበረው። በወቅቱ የቡድኑ ተጫዋች የነበረው የማይክል ኦወን ማልያ ነበረው።

አንድ ቀን ያሬድ ቴሌቪዥን እያየ ሳለ የለበሰውን ቲሸርት (ማልያ) የሚመስል የለበሱ ከአሥር በላይ ሰዎች አይቶ ይደነቃል።

በዙሪያው የነበሩትን ሲጠይቅ ሊቨርፑል የሚባል የእግር ኳስ ቡድን መሆኑን ይነግሩታል።

ከዚያች ቀን አንስቶ ያሬድ የሊቨርፑል ደጋፊ ሆነ፤ ፍቅራቸው በቃል ኪዳን ባይታሰርም በተጻፈ ሕግ ውለታ ባይገባለትም የፀና ሆነ።

ያኔ ነበር፣ ያሬድ ገና የ9 ዓመት ልጅ እያለ ከጋዜጣ፣ ከመጽሔትና ከተለያዩ ቦታዎች የሊቨርፑልን ዓርማ፣ ምስሎችን፣ ተጫዋቾችና ሊቨርፑል ይኑርበት እንጂ ያገኘውን ነገር ሁሉ እየሰበሰበ በመኝታ ቤቱ ግድግዳ ላይ መለጠፍ ጀመረ።

አሁንም መኝታ ቤቱ መጠነኛ የሊቨርፑል ሜዳ ወይም መኖሪያ እንጂ የያሬድ ቦጋለ ማደሪያም አይመስልም።

ያሬድ ግን የራሱን መኝታ ቤት በሊቨርፑል ከማሳመሩ ባሻገር ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ያዳበረው ችሎታው ይበልጥ ትኩረት ይስባል።

ያሬድና የግድግዳ ላይ ዕሎቹ

ቀለማትን ደባልቆ የሳሎኑን፣ የኮሪደሩን፣ የመመገብያ ክፍሉን ግድግዳዎች ሳይቀር በተለያዩ ዲዛይኖች ማስዋብ ጀመረ።

እጁን በግድግዳው ላይ ከማሳረፉ በፊት ግን በዩትዩብ በመታገዝ የሥዕልን መሠረታዊ እውቀት ቀሰመ። ከዚያም ቁሳቁሶችን ለማሟላት ሲፈልግ በኢትዮጵያ ለግድግዳ ማስዋብያ ታስበው የተሠሩ ቀለማትና ብሩሾችን ማግኘት ተቸገረ።

ከአገር ውጪ ይኖር የነበረ ጓደኛውን ሲያማክረው አማዞን በተባለው ኢንተርኔት መገበያያ ድረ ገፅ የሚፈልገውን ሁሉ አዞ ወደ ኢትዮጵያ ላከለት።

ያሬድ ቀጥሎ የሆነውን ሲናገር "ሁሉ ነገር ሲሟላልኝ ጊዜ የተማርኩትን ለመተግበርና ውስጤ የነበረውን ለማንፀባረቅ እጆቼን በግድግዳዎቹ አነሳሁ" ይላል።

በመቀጠልም ሥራዎቹን በፌስቡክና ኢንስታግራም ላይ ማጋራት ጀመረ። የሚያውቁትም ሥራዎቹን አጋሩለት፣ ብዙዎች እየፃፉ የእነርሱንም ቤት እንዲያስውብላቸው ጠየቁት።

ከዚያም ቅዳሜ፣ እሁድና የእረፍት ቀኖቹ ወደ ሰዎች ቤት በማቅናት በግድግዳ ላይ መሳልን ተያያዘው።

ሳያስበውም ያኔ በዘጠን ዓመቱ እንደ ጨዋታ ጀምሮ የለቀቀው ልምድ አሁን ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ ሆነለት።

ያሬድ በሚስልበትም ወቅት ሆነ ሥዕሉን ግድግዳው ላይ አስፍሮ ከጨረሰ በኋላ በቪድዮና በፎቶግራፍ ለማስታወሻ ያስቀራል።

ምክንያቱ ደግሞ አንዴ የሳላቸውን በማጥፋት ሌላ የመሳል ባህሪ ስላለው መሆኑን ይናገራል።

ከአያቱና ከታላቅ እህቱ ጋር የሚኖረው ያሬድ፣ "አንዳንዶቹን እነርሱ ስለሚወዷቸው ሳይነኩ የተቀመጡ ሥዕሎች አሉኝ" ይላል።

ያሬድ ከቤተሰቦቹ የሚያገኘውን ማበረታቻና ድጋፍ ሲገልጽ "ይህን ብታስተካክለው፣ ይህን ደግሞ እንዲህ ብታደርገው እያሉ ሥራዬን ከማዳነቅ አልፈው ወደማገዝ ሁሉ ደርሰዋል" ሲል ቤተሰቡን ያመሰግናል።

ያሬድ የመሳል ችሎታውን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ ያዳብረው እንጂ ልጅ እያለ እንደማንኛውም ልጅ ሥዕሎችን በመስኮት ላይ አስደግፎ በመሳል መጀመሩን ያስታውሳል።

ከጊዜ በኋላ ግን እነዚያን ሥዕሎች ቀስ በቀስ መጠናቸውን በማሳደግ አሁን የደረሰበት የግድግዳ ወይም 'ዎል አርት' ወደ መሥራት ተዘዋወረ።

ያሬድ እንደሚለውም "ዛፍ፣ ሰው ምናምን እያዩ መሥራት ወይም ሌሎች ነገሮችን መሳልና ስኬች ማድረግ አልችልም። ግድግዳ ላይ ለኢንቲሪየር ዲዛይን የሚሆኑ ሥዕሎችን ግን በትልቁና ትንንሽ ይዘታቸውን [ዲቴሎችን] ሳይቀር ጠንቅቆ መሥራት እችልበታለሁ፤ ለዚያም ነው ብዙ ሰዎች ቤታቸው ድረስ የሚጠሩኝ" ይለናል።

ያሬድ በልጅነቱ የነበረውን የሥዕል ተሰጥኦ ዝም ብሎ ይዞ አለመቀመጡን ይናገራል።

"ኤሪክሰን ለተባለው የቴሌኮምዩኒኬሽን ድርጅት ተቀጥሬ እሠራ በነበረበት ወቅት ፊልድ ስለምንወጣ፣ ለሰዓታት በመኪና እንጓዝ ነበር፤ እናም ያኔ መኪና ውስጥ ዝም ብዬ ስስል ትዝ ይለኛል. . . አጥብቄ አልያዝኩትም ነበር" ይላል።

አሁን ግን ያሬድ ከራሱ ቤት ግድግዳ አልፎ የተለያዩ ምግብ ቤቶችና ሆቴሎችን ግድግዳ በሥዕል ያስውባል።

ያሬድ ሁሌም ቢሆን በቅድሚያ ማስዋብ የሚመርጠው የራሱን ግድግዳዎች መሆኑን ይናገራል።

ምክንያቱንም ሲያስረዳ "ስፈልግ በቁምጣ፣ ቲሸርቴን አውልቄ ወይም እያረፍኩና ሙዴን እየተከተልኩ እሠራለሁ። ለሌላ ሰው ስሠራ ግን ከአለባበሴ አንስቶ ማስረከብ እስካለብኝ ሰዓት ድረስ እገደባለሁ፤ በተለይ በኮቪድ ምክንያት አንዳንዴ ማሟላት ያሉብኝ ነገሮች ብዙ ናቸው እናም በዚያ ምክንያት ትንሽ ያስተጓጉለኛል፣ ሆኖም ግን የሥራው ፀባይ በመሆኑ ተቀብዬዋለሁ" ይላል።

ያሬድ የሥዕል ሥራዎቹን እየተዘዋወረ ሲሰራ ከኮቪድ ባሻገር የሚያስቸግረው የደንበኞቹ ሃሳብ መለዋወጥ ነው።

ደንበኞች አንዳንዴ ሥራውን ካዘዙት በኋላ ሃሳብ መቀየራቸው ወይም አስጠፍተው ድጋሚ ማሠራታቸው ሥራውን በፕሮግራም እንዳያከናውን እንደሚያደርገው ይናገራል።

አክሎም "እንደዚህ ዓይነት ሥራ እየተለመደ ሲመጣ ሰዎችም የሚፈልጉትን ጠንቅቀው በማወቅ ትዕዛዛቸውን፣ ፍላጎታቸውንና ጥያቄዎቻቸውን እንደሚያስማሙ ተስፋ አድርጋለሁ" ሲል ተስፋውን ይገልጻል።

ያሬድ አልፎ አልፎ የሚጠየቀው ሥራ ብቻውን ሊወጣው የሚችለው ዓይነት ባለመሆኑ በአሁን ጊዜ ሥራ አጥተው የተቀመጡ አብረውት የተማሩ የሜካኒካል ኤንጅኒሪንግ ምሩቅ ጓደኞቹን አሠልጥኖ ተጋግዘው እንዲሠሩ የማድረግ ፍላጎት እንዳለው ይገልፃል።

የያሬድ ቦጋለ ህልም የሊቨርፑል ተጫወቾች መኝታ ቤቱን እንዲያዩለትና አድናቆታቸውን እንዲያጋሩት ብቻ ሳይሆን "ቀስ ብዬ ብዙ ወጣቶችን አሠልጥኜ ሥራ ፈጣሪ መሆን እፈልጋለሁ። ደግሞም በዚህ ሥራ ብዙ ዕድሎች እንደሚከፈቱልን እርግጠኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ከውጪ አገር ተገዝተው የሚለጠፉ እንጂ እንደኔ በቀለም ጊዜ ተወስዶባቸው ግድግዳ የሚያስውቡ ሰዎች የሉም" በማለት ሃሳቡን ያጠናቅቃል።