ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጥንት ምስሎችን ነፍስ የሚዘራባቸው ወጣት
የ23 ዓመት ወጣት ነው፤ ትውልና እድገቱ ደግሞ ነቀምት- ገመቺስ ተሾመ። በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን የያዘው ገመቺስ ለቪዲዮና ለፎቶ ጥበብ ለየት ያለ ፍቅር አለው።
በአሁኑ ጊዜ ለተለያዩ ድርጅቶች ዓርማቸውን ዲዛይን በማድረግ በመስራት ገቢ ያገኛል። ለፎቶና ለቪዲዮ ጥበብ ያለውን ፍቅር ወደ ክህሎት አሳድጎት ደግሞ የቆዩ ስዕሎች ዳግም ነፍስ እንዲዘሩ ባለጥቁርና ነጭ ምስሎችን ወደ ባለቀለም ምስል የመቀየር ሥራ ላይ እየተሰማራ ነው።
ይህ የቆዩ ምስሎችን ወደ ባለቀለም የመቀየር ጥበብ በኢትዮጵያ ውስጥ እምብዛም አልተለመደም የሚለው ገመቺስ ስዕሎቹ ላይ ዳግም ነፍስ መዝራት ብቻ ሳይሆን ታሪካቸውም በእድሜ እኩዮቹ ልብ ውስጥ እንዲቀር እንደሚፈልግ ይናገራል።
ገመቺስ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ እነዚህ የድሮ ምስሎችን ወደ ባለ ቀለም ፎቶነት የመቀየር ጥበብ ቀለም የመቀባት (ከለራይዜሽንና እና ሪተች) እንደሚባል ነግሮናል።
"ይህ ማለትም ከረዥም ጊዜ በፊት የተነሱ ፎቶዎች ጥቁርና ነጭ ሲሆኑ እንዲሁም ጥራታቸው በጣም የወረደ ነው፤ ታዲያ እነዚያን በዘመናዊ መልኩ ቀለም በመቀባት ነፍስ መዝራት ማለት ነው ሪተች ወይንም ከለራይዜሽን" ይላል ገመቺስ።
ምስሎቹ በዚህ መልክ ዳግም መሠራታቸው ለባለፎቶዎቹ ዳግም ትዝታቸውን እንዲያድሱ፣ የሚወዱት ሰው ምስል ለረዥም ጊዜ እንዳማረበት እንዲቆይ እንዲሁም በወጣቱ ትውልድ ተቀባይነት እንዲኖረው ያስችለዋል ባይ ነው።
ገመቺስ ራሱን ሲጠራ ሲኒማቶግራፊ ባለሙያ ነኝ በማለት ነው። በተለያዩ የግል የቴሌቪዥን ጣብያዎች በዚህ ሙያ እንደሚሰራም ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል። ከልጅነቱ ጀምሮ የዚህ ጥበብ ፍላጎት እንደነበረው የሚናገረው ገመቺስ ክህሎቱን ለማሳደግ የተለያዩ ነገሮች ማድረጉን ይናገራል።
"በዚህ ዘርፍ ታዋቂነትንና ልምድ ያላቸውን ሰዎች በማግኘት ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉኝ እጥር ነበር ሁል ጊዜ" ይላል ገመቺስ። ከዚህ በተጨማሪም እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ወደ ኢንተርኔት ጓዳ ብቅ በማለት በዚህ ሙያ ላይ የተሰሩ ማስተማሪያዎችን (ቱቶሪያልስ)፣ አጫጭር ስልጠናዎችን በመውሰድ ራሱን በእውቀት ማደርጀቱን ይናገራል።
ገመቺስ በአሁኑ ወቅት የማንኛውንም ግለሰብ ምስሎች ወደ ባለቀለም ከመቀየር ይልቅ ስምና ዝናቸው በማህበረሰቡ ዘንድ ገናና የሆኑ ሰዎችን የቆዩ ምስሎች ማደስ ያስደስተዋል።
"እኔ እነዚህ የመረጥኳቸው ሰዎች በባህልም ይሁን በሀይማኖት በዚህ በአሁኑ ትውልድ ታሪካቸው እየተረሳ የመጣ ግለሰቦች ናቸው። እኔ ባለኝ ሙያ የቀድሞውን ትውልድ ከአሁኑ ትውልድ ጋር ለማስተዋወቅ ስል ነው የጀመርኩት" ይላል።
እስካሁን ነፍስ ከዘራባቸው ስራዎችም የኦነሲመስ ነሲብን ስራ በጣምን እንደሚወደው ይናገራል።
ኦነሲሞስ ነሲብ በልጅነታቸው ለስምንት ጊዜ ያህል በባርነት መሸጣቸው ይነገራል፤ በኋላም ከባርነት ነፃ ከወጡ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ የተለያዩ መጻህፍትን በመተርጎምና በመጻፋቸው ይታወቃሉ።
"ኦነሲሞስ እኔ ጋር በጣም ትልቅ ቦታ ነው ያለው። የመጀመሪያ ስራዬም ነው" የሚለው ገመቺስ፣ በሌላ ስማቸው ሂካ አዋጂ የሚባሉት እኚህ ሰው በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ብዙ ታሪክ እንዳላቸው ይናገራል። እኚህ ግለሰብ መፍሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ የተረጎሙ ሰው በመሆናቸው ይታወቃሉ።
ገመቺስ የወደፊት ሕልሙንም ሲናገር የቆዩ የታሪክ ድርሳናትን በማገላበጥ እና በማንበብ የቀደሙ የታሪክ ባለውለታዎችን ፎቶ ወደ ባለቀለም ምስል በመቀየር ከአሁኑ ትውልድ ጋር ለማስተዋወቅ ይፈልጋል፤ በዚህ ረገድ "ትልቅ ስራ" እንደሚጠብቀውም ይናገራል።