ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖሊስ ኢትዮ-እስራኤላውያንን ጨምሮ ዜጎችን ሰልሏል መባሉን እስራኤል ልታጣራ ነው
የእስራኤል ፖሊስ ከኢትዮጵያ የሄዱ ቤተ እስራኤላውያንን ጨምሮ የታዋቂ ዜጎችን ስልክ ያለሕጋዊ ፈቃድ ጠልፏል የሚለውን ክስ የሚያጣራ ኮሚሽን በእስራኤል መንግሥት እንደሚቋቋም ተገለጸ።
የስልክ ግንኙነትን የሚፈትሽ መተግበሪያ (ስፓይዌር) ያለ ፈቃድ በመጠቀም የቀድሞው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ልጅን ጨምሮ የባለሥልጣናትን፣ ተቃዋሚዎችን እና የጋዜጠኞችን ስልክ መሰለሉ 'ካልካስት' በተባለ ጋዜጣ ተዘግቧል።
የኔታንያሁ የሙስና ክስ ውስጥ የተካተተ ምስክር ስልክም እንደተጠለፈ ተገልጿል።
የኔታንያሁ ልጅ እና በሙስና ክስ ላይ ምስክር የሆኑም ስልካቸው መጠለፉ ቢገለጽም፤ በስለላ የተገኘው መረጃ በፍርድ ቤት እንደማስረጃ ስለመቅረቡ አልታወቀም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት "ይህ ዘገባ እውነት ከሆነ ከባድ ጥፋት ነው የተፈጸመው" ብለዋል።
ጋዜጠኞች እንደሚሉት የእስራኤል ፖሊሶች ፔጋሰስ የተባለውን የስለላ መተግበሪያ ነው የተጠቀሙት።
በእስራኤሉ ጋዜጣ በወጣው ዘገባ መሠረት የበርካታ እስራኤላውያን ስልክ በፖሊስ ያለ ፈቃዳቸው ተጠልፏል።
ሕጋዊ ምርመራ ባልተከፈተባቸው ሰዎች እንዲሁም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ስለላው መከናወኑም ተጠቁሟል።
ስለላ ሲካሄድባቸው ነበር ከተባሉት መካከል የአገሪቱ የትራንስፖርት፣ የገንዘብና የፍትሕ ሚኒስትሮች ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን-እስራኤላውያን እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች መብት ተሟጋቾችም እንደተሰለሉ ተገልጿል።
በእስራኤል ውስጥ የሚገኙ ተቃዋሚዎች ብሎም የኔታንያ፣ መቫስረት ዛየን፣ ኪርያት አታ እና ሆሎን ከንቲባዎችም ያለ ፈቃዳቸው እየተሰለሉ ነበር ተብሏል።
ፔጋሰስ መተግበሪያን ያመረተው የእስራኤሉ ኤንኤስኦ ሲሆን፤ ተቋሙ በመላው ዓለም ለአምባገነን መሪዎች የስለላ መተግበሪያ በመሸጥ ይወነጀላል።
ድርጅቱ በበኩሉ መተግበሪያውን አንዴ ከሸጠ በኋላ ክትትል እንደማያደርግና የእስራኤል ዜጎችን ለመሰለል እንደማይውል ገልጿል።
የእስራኤል ፖሊስ ያለ ዜጎች ፈቃድ ሰልሏል የሚለውን ዘገባ በተመለከተ ግን እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።
ፔጋሰስ የተባለው መተግበሪያ ከግለሰቦች ስልክ አጭር የጽሑፍ መልዕክት፣ ምስል፣ ኢሜል፣ የተቀረጸ ድምጽ እና የስልክ ንግግር መጥለፍ ያስችላል።
"ፔጋሰስ ሽብርና ሌሎች ወንጀሎችን ለመዋጋት ከሚያስችሉ መተግበሪያዎች አንዱ ነው። ነገር ግን መተግበሪያው የእስራኤል ዜጎችንና ባለሥልጣናትን እንዲሰልል አልተሠራም" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት።
ምክትል ዐቃቤ ሕግ አሚት ሜሪ ጉዳዩን እየተከታተሉት እንደሚገኙና ለሕዝቡ ምላሽ እንደሚሰጥም አክለዋል።
ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ "ዴሞክራሲያችንን ልናጣ አይገባም። ፖሊሳችንን ልናጣ አይገናም። ሕዝባችንም በፖሊስ ላይ እምነት እንዲያጣ አንፈልግም" ብለዋል።
የሕዝብ ደኅንነት ሚኒስትር ኦማር ባርሊዝ፤ ጉዳዩን የሚመረምረው ኮሚሽን ጡረታ በወጡ ዳኛ እንደሚመራና ማንኛውንም ሰው ለምስክርነት የመጥራት መብት እንዳለው አስረድተዋል።