ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዱባይ ልዕልት ስልክ ቁጥር በምስጢር መንታፊው ፔጋሰስ ዝርዝር ውስጥ ተገኘ
የዱባይ ልዕልት ላቲፋ ስልክ በምስጢር መንታፊው ፔጋሰስ ሶፍትዌር ስም ዝርዝር መገኘቱ ይፋ ሆነ፡፡
የዱባይ መሪ ሴት ልጅ ልዕልት ላቲፋ እንዲሁም ሌላኛዋ ልዕልት ሐያ ቢንት አል ሑሰይን ስልኮቻቸው ከዚህ ምስጢር መንታፊ ሶፍትዌር ዝርዝር ውስጥ ተገኝቷል፡፡
ባለፈው የካቲት አጋማሽ በተሰጠራጨ የቢቢሲ ፓኖራማ ዘገባ ልዕልት ላቲፋ በቤተሰቧ በአስገዳጅ የቁም እስር ላይ እንደምትገኝ የገለጸችበት ቪዲዮ ለዓለም ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡
ልዕልት ሐያ በበኩሏ በፈረንጆቹ 2019 ለሕይወቷ በመስጋት ከዱባይ ወጥታ በዩኬ ጥገኝነት መጠየቋ ይታወሳል፡፡
የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የሁለቱን ልዑላን ክሶች ውድቅ አድርጓል፡፡
ከሰሞኑ መቀመጫውን በእስራኤል ያደረገውና በምህጻሩ ኤንኤስኦ ግሩፕ ተብሎ የሚጠራ አንድ ኩባንያ ያመረተው ፔጋሰስ ሶፍትዌር እስከዛሬ የዝነኛ ሰዎችን ስልኮች ሲጠልፍ እንደነበር ተደርሶበት መነጋገርያ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ስልካቸው ሳይጠለፍ አልቀረም የተባሉ 50ሺህ የዓለማችን ዕውቅ ሰዎች ስም ዝርዝርም ለሚዲያዎች ሾልኮ ደርሷል፡፡
ትናንት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ስልክ ቁጥር ከዝርዝሩ መገኘቱ የብዙ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ትልቁ ዜና ሆኖ ነበር
ስልካቸው ምናልባት ተጠልፎባቸዋል ተብለው ትናንት ቁጥራቸው ይፋ ከሆኑት ግለሰቦች መሀል የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ፣ የኢራቁ ባራም ሳሊህ እንዲሁም የፓኪስታን፣ የግብጽና የሞሮኮ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ይገኙበታል።
የሞሮኮ ንጉሥ ስልክም በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተገኝቷል።
የነዚህ ሁለት የዱባይ ልዑላን ስም በዚህ ምስጢር መንታፊ ሶፍትዌር ስም ዝርዝር ውስጥ መገኘቱ ምናልባት እስከዛሬም ምስጢራቸው ሲበረበር እንደነበር አንድ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የፔጋሰስን አምራች ኩባንያ ከፍተኛ የሰዎችን መብት ጥሰት ፈጽመኻል ሲል ከሶታል፡፡
ኩባንያው ግን ሶፍትዌሩን ያመረትኩትና የምሸጠውም ለወታደራዊና ደኅንነት ጉዳዮች ነው ይላል፡፡
አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣን ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት መንግሥት የፔጋሰስን ጉዳይ የሚያጣራ አንድ ቡድን አቋቁሟል፡፡
ልዕልት ላቲፋ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ እንደተናገረችው ከዱባይ ለማምለጥ በሽሽት ላይ ሳለች ተደርሶባት በድጋሚ በገዛ ቤተሰቦቿ የቁም እስረኛ ተደርጋለች፡፡
ልዕልት ሐያ በበኩሏ በቀድሞ ባሏ ጠለፋ ስቃይና ድብደባ እንደደረሰባት ተናግራ ነበር፡፡
ልዕልት ሐያ ወደ ዩኬ ጠፍታ የመጣችው በ2019 ሲሆን ሁለት ልጆቿም አብረዋት ነበሩ፡፡
የልዕልት ላቲፋና ልዕልት ሐያ በዚህ ምስጢር መንታፊ ሶፍትዌር ዝርዝር ስልክ ቁጥራቸው መካተቱ ምናልባት እንቅስቃሴያቸው ለረዥም ጊዜ በምስጢር ለሦስተኛ ወገን ሲደርስ እንደነበር አመላካች ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ፔጋሰስ መንታፊ ሶፍትዌር የሰዎችን የጥሪ፣ የምሥል፣ የጽሑፍ፣ የተንቀሳቃሽ ምሥልና ያሉበትን ቦታ አንድም ሳያስቀር ለሦስተኛ ወገን የሚያቀብል ነው፡፡