ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ አቅርቦት የውጭ ኃይሎች ሚና አላቸው - አምባሳደር ቲቦር ናዥ
የዓለም ኃያላን መንግሥታት በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት እንዲቆም ሊረዱ ይችላሉ ሲሉ የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ገለጹ።
እነዚህ መንግሥታት ግጭቱን ለማስቆም መርዳት የሚችሉት በጦር መሳሪያ ንግድ ውስጥ በሚጫወቱት ሚና ነው በማለት አምባሳደር ቲቦር ናዥ ለቢቢሲ ኒውስደይ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ረዳት ኃላፊ በመሆን የሰሩት አምባሳደር ቲቦር ኒዥ ተፅእኖ ፈጣሪ የሆኑት እንደ አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ቻይና፣ ቱርክ እና የባሕረ ሰላጤው አገራት " በታሪክ ውስጥ ከተሰቱ ጦርነቶች አላስፈላጊ የሚባለውን ጦርነት አቁሙ በማለት መናገር ይችላሉ" ብለዋል።
አክለውም "እውነት እንናገር ከተባለ የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ትጥቃቸውን ከተወሰነ ቦታ ስለሚያገኙ ትኩረት ይሰጣሉ" በማለት ያስረዳሉ።
በኢትዮጵያ ዓመት ባስቆጠረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ በመቶ ሺዎች ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
ጦርነቱ የተቀሰቀሰው ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24 ሲሆን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ ክልል በሚገኙ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ ጥቃት እንዲሰነዘር ትዕዛዝ በሰጡበት ወቅት ነው።
መንግሥታቸው ይህን ያደረገው በአገሪቱ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ወታደራዊ ካምፕ ላይ ለደረሰው ጥቃት ምላሽ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሓትን በአሸባሪነት ቢፈርጅም፤ ህወሓት በበኩሉ የትግራይ ክልል ሕጋዊ አስተዳዳሪ ነኝ ይላል።