ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በትዕግስት ገዛኸኝ አገኘች

ትዕግስት ገዛኸኝ በፓራሊምፒክ ውድድር ላይ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ አስመዘገበች።

ይህ በአትሌት ትዕግስት የተገኘው የወርቅ ሜዳሊያ በኢትዮጵያ የፓራሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ውስጥ አገሪቱ ያገኘችው የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳልያ ነው።

በጃፓን፣ ቶኪዮ እየተካሄደ ባለው የፓራሊምፒክ ውድድር ላይ በአንድ ሺህ አምስት መቶ ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ አንደኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው የወርቅ ሜዳሊያ ተመዝግቧል።

በዚህ ውድድር ከትዕግስት በመከተል አሜሪካዊት አትሌት ሁለተኛ እንዲሁም ከአፍሪካ ቱኒዚያዊት ደግሞ በሦስተኛነት አጠናቀዋል።

በዘንድሮው ፓራሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ሦስት አትሌቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ባለፈው ማክሰኞ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም በተጀመረው በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ በትዕግስት ገዛኽኝ ባገኘችው የወርቅ አማካይነት በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ላይ ከተወዳዳሪ አገራት መካከል የ35ኛ ደረጃን ለጊዜው ይዛለች።

በዚህም በቶኪዮው የፓራሊምፒክ ውድድር ላይ ከሚሳተፉ የአፍሪካ አገራት ከደቡብ አፍሪካ፣ ከአልጄሪያ፣ ከቱኒዚያ እና ከናይጄሪያ በመቀጠል አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክ የተሳተፈችው እስራኤል፣ ቴል አቪቭ ውስጥ እ.አ.አ በ1968 በተካሄደው ውድድር ላይ ነበር።

በ2012 በተካሄደው ፓራሊምፒክ ላይ አትሌት ወንድዬ ፍቅሬ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን የብር ሜዳልያ አስመዝግቦ ነበር።

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የብር ሜዳልያ ያገኘችው በ2016 በሪዮ ደ ጄኔሮ የወንዶች 1500 ሜትር ሩጫ በአትሌት ታምሩ ደምሴ አማካይነት ነው።

የቶኪዮ ኦሊምፒክን ጨምሮ ኢትዮጵያ በፓራሊምፒክ ውድድር እስካሁን ስምንት አትሌቶችን አሳትፋለች።

ዛሬ ትዕግስት ገዛኸኝ ያስመዘገበችው የወርቅ ሜዳልያ በፓራሊምፒክ ታሪክ ለኢትዮጵያ ትልቁና ቀዳሚው ውጤት ነው።

ማክሰኞ ነሐሴ 18/2013 ዓ.ም የተጀመረው የቶኪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር ለ13 ቀናት ይካሄዳል።

ኢትዮጵያን በፓራሊምፒክ ውድድር የሚወክሉት አትሌት ታምሩ ከፍያለው፣ አትሌት ገመቹ አመኑ እና አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ ናቸው።

ቱኒዚያ ላይ በ1500 ሜትር በተደረገው የማጣሪያ ውድድር አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ 4:31:53 በመግባት አንደኛ በመሆን ማጠናቀቋ ይታወሳል።