አቡበከር ሼካው፡ የቦኮ ሀራሙ መሪ መሞቱን ተፎካካሪው የታጣቂ ቡድን ገለጸ

የናይጄሪያው ታጣቂ ቡድን ቦኮ ሃራም መሪ አቡበከር ሼካው ራሱን ማጥፋቱን ተቀናቃኝ እስላማዊ ታጣቂዎች በተቀረጸ የድምጽ መልዕክት ገለጹ።

የዜና ወኪሎች ባገኙት ድምጽ እስላሚክ ስቴት ዌስት አፍሪካ ፕሮቪንስ (ኢስዋፕ) እንዳመለከተው በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተደረገ ውጊያ ተከትሎ ሼካው ፈንጂዎችን በራሱ ላይ በማፈንዳት ህይወቱ አልፏል።

ሼካው ባለፈው ወር ህይወቱ እንዳለፈ የተዘገበ ሲሆን ከዚህ በፊት መገደሉም ተገልጾ ነበር።

ቦኮ ሀራም ሆነ የናይጄሪያ መንግሥት የመሪውን መሞት በተመለከተ ያሉት ነገር የለም።

የድምጽ መልዕክቱ ምን ይላል?

ቀኑ ባልተገለጸበት የድምጽ ቀረጻ የኢስዋፑ መሪ አቡ ሙስዓብ አል-ባራዊ ነው ተብሎ በታሰበው ድምጽ ሼካው "ፈንጂ በማፈንዳት ራሱን አጠፋ" ብሏል።

"ሼካው በምድር ላይ ከመዋረድ ይልቅ ከሞት በኋላ ባለ ሕይወት መዋረድን መረጧል" ብሏል።

ባለፈው ወር በተፈጠረ ግጭት የሼካውን ህይወት ማለፉን ዘገባዎች መሰራጨታቸውን ተከትሎ የናይጄሪያ ጦር ምርመራ እንደሚያደርግ ተናግሮ ነበር።

የመከላከያ ሠራዊቱ ቃል አቀባይ ብርጋዴር ጄኔራል መሃመድ የሪማ በወቅቱ ለቢቢሲ ሠራዊቱ የተከሰተውን ነገር እየመረመረ ሲሆን ትክክለኛ ማረጋገጫ እስኪያገኝ ድረስ መግለጫ አይሰጥም ብለዋል።

ከደህንነት ኤጀንሲዎች ጋር የቅርብ ትስስር ያለው አንድ ጋዜጠኛ እንደተናገሩት ኢስዋፕ በሰሜናዊ ምስራቅ ናይጄሪያ በሚገኘው ሳምቢሳ ጫካ ውስጥ የሚገኙ የቦኮ ሃራም ቦታዎችን ሲያጠቃ የሼካው ህይወት አልፏል።

ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ጊዜ ህይወቱ ማለፉ ሪፖርት ተደርጓል።

አቡበከር ሼካው ማነው?

የቡድኑ መስራች እአአ በ 2009 በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ከሞተ በኋላ ሼካው የቦኮ ሃራምን መንበር ተረክቦ በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ አደገኛ ወደሚባል ቡድን ተቀይሯል።

በሼካው ስር ቦኮ ሃራም በክልሉ የቦምብ ፍንዳታዎችን፣ እገታዎችን እና እስር ቤቶችን መስበርን በተደጋጋሚ አካሂዷል። ቦኮ ሃራም እአአ ከ 2014 ጀምሮ በሸሪዓ ህግ የሚመራ እስላማዊ መንግስት ለመፍጠር ከተሞችን መቆጣጠር ጀመረ።

ዕድሜው ከ 40ዎቹ መጀመሪያ እስከ 40 ዎቹ አጋማሽ እንደሆነ የሚታመነው ሼካው፤ ከኦሳማ ቢን ላደን ጋር በሚያመሳስለው መልኩ በፕሮፓጋንዳ ቪዲዮዎቹ ደም አፋሳሽ ጂሃዳዊ ዘመቻን ደግፏል።

በአንድ የ 2012 ቪዲዮ ላይ "መግደል ያስደስተኛል ... ዶሮዎችን እና በጎችን በማረድ ደስ እንደሚለኝ ማለት ነው" ብሏል።

መንበሩን ከተቆጣጠረ በኋላ ከ 30,000 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል።

ቡድኑ እአአ በ 2014 በቦርኖ ግዛት ቺቦክ ከሚባል ትምህርት ቤት በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶችን አግቶ ከወሰደ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሙ ገኗል።

በወቅቱ ታፍነው የተወሰዱት አብዛኛዎቹ ተማሪዎች አሁንም አልተመለሱም።

አሜሪካ ሼካውን "ዓለም አቀፋ አሸባሪ" ብላ ለማሰወጅ ጊዜ ያልፈጀባት ሲሆን ያለበትን ለሚጠቁም 7 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ አስለው ብላለች።

የሸካው አጀንዳ በጣም ጽንፈኛ መሆኑን ተከትሎ በእስላሚክ ስቴት ተቀባይነት ያጣ ሲሆን ከቦኮ ሃራም ተገንጥሎ በ 2016 ኢስዋፕን ለመመስረት ምክንያት ሆነ።

ቦኮ ሀራም በቀጣይ ምን አማራጭ አለው?

የሼካው ሞት መረጋገጥ የቦኮ ሃራምን መጨረሻ ስለማሳየቱ ምንም ማረጋገጫ የለም ሲሉ ተንታኞች ይናገራሉ።

ኢስዋፕ ከቦኮ ሃራም ተለይቶ መውጣቱን ተከትሎ ቦኮ ሃራምን ተከትሎ በክልሉ ዋነኛው አመጺ ቡድን እንዲሆን አድርጎታል።

አንዳንዶች የሼካው ሞት በሁለቱ ቡድኖች መካከል የከረረው ፉክክር ሊያቆም ይችላል ብለው ይተነብያሉ። ኢስዋፕም የቦኮ ሃራምን ተዋጊዎችን ለመውሰድ ያስችለዋል ይላሉ።