ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዩክሬን ብሔራዊ ቡድን ማልያ ሩስያን አስቆጣ
የዩክሬን የእግር ኳስ ብሄራዊ ቡድን ማልያ ላይ በሩሲያ ቁጥጥር ስር የምትኘው ክሬሚያን ያካተተ ካርታ መካተቱን ተከትሎ ሞስኮ ቁጣዋን እየገለጸች ነው።
ዩክሬን በዩሮ 2020 የምትጫወትበትን ማልያ ይፋ ያደረገች ሲሆን ማልያውም የከፍተኛ ውዝግብ ምክንያት የሆነችው ክሬሚያን ያካተተ ነው። በማልያውም ላይ ‘ድል ለዩክሬን’ የሚል መልዕክት ተጸዕፏል።
ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2014 ነበር የክሬሚያን አካባቢ ከዩክሬን ወስዳ የራሷ ያደረገችው። በዚህም ሩሲያ አካባቢውን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥረው ቢሆንም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግን እስካሁን እውቅና አልሰጠም።
የዩክሬንን ብሄራዊ ቡድን መለያ በተመለከተ መልዕክት ያስተላለፉ አንድ የፓርላማ አባል ጉዳዩን ‘’ፖለቲካዊ ትንኮሳ’’ ነው ብለውታል።
የዩክሬን እግር ኳስ ማህበር ኃላፊው አንድሬይ ፓቬልኮ ነበሩ ትናንት እሁድ ዕለት የብሄራዊ ቡድኑን መለያ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ያስተዋወቁት። የአውሮፓ እግር ኳስ ውድድር ወይም ዩሮ 2020 ከቀናት በኋላ ይጀመራል።
በቢጫው የብሄራዊ ቡድኑ መለያ ፊትለፊት ላይ በነጭ መስመር የአገሪቱን ክልል የተገለጸ ሲሆን ክሪሚያንም ያካተተ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በተገንጣይ ቡድኖች ቁጥጥር ስር የሚገኙት ዶኔስክ እና ሉጋንስክም ጭምር በማልያው ላይ እንዲካተቱ ተደርጓል።
በማልያው ጀርባ ደግሞ ‘ድል ለዩክሬን’ የሚል መፈክር ሰፍሯል። ይህ መፈክር በአውሮፓውያኑ 2014 ሩሲያን የሚደግፉት ፕሬዝደንት ቪክቶር ያኑኮቪችን ከስልጣን ያስወገዱት ሰልፈኞች በተደጋጋሚ ይጠቀሙበት የነበረ ነው።
‘’ይህ የዩክሬን ሁኔታ ተጫዋቾቹ ጥንካሬ እንዲያገኙና ለሁሉም ዩክሬን እንዲጫወቱ እንደሚያደርግ እምነት አለን’’ ብለዋል የዩክሬን እግር ኳስ ማህበር ኃላፊው አንድሬይ ፓቬልኮ።
ነገር ግን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ የብሄራዊ ቡድኑን መለያ ተችተዋል። ‘’ብሄራዊ ቡድኑ የሩሲያ አካል የሆነችውን ክሪሚያን ማካተቱ ሊሆን የማይችልን ነገር እንደ ማሰብ ነው’’ ብለዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ዲሜትሪ ስቪሽኮቭ በበኩላቸው የብሄራዊ ቡድኑ መለያ ‘’ከነጭራሹ ተገቢ ያልሆነ’’ ነው ያሉ ሲሆን የየዑሮ 2020 አዘጋጆችና የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።
የዘንድሮው ዩሮ 20202 በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተለያዩ 11 የአውሮፓ ከተሞች ከሰኔ 4 ጀምሮ ለአንድ ወር ይካሄዳል። ውድድሩን ከሚያስተናግዱት ከተሞች መካከል ደግሞ የሩሲያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ትገኝበታለች።