ስኮትላንድ ነዋሪ አልባውን ደሴት የሚጠብቅ ሠራተኛ እያፈላለገች ነው

ስኮትላንድ ውስጥ የሚገኝ አንድ ነዋሪ አልባ ደሴትን የሚጠብቅ ሠራተኛ እየተፈለገ ነው።

አይል ማርቲን የተባለው ደሴት ውስጥ የሚኖር ሰው የለም። የሚቀጠረው ሠራተኛ ኃላፊነት ደሴቱን መንከባከብና ለጎብኚዎች ዝግጁ ማድረግ ይሆናል።

ከሰዎች ራቅ ብለው በብቸኝነት መኖር ለሚሹ ሰዎች ይህ ሥራ ሁነኛ አማራጭ ይመስላል።

ለዚህ ሥራ የሚያመለክቱ ሰዎች ብቻቸውን ወይም ከውሃ አጣጫቸው ጋር ደሴቱ ውስጥ መኖር ይፈቀድላቸዋል።

በደሴቱ ውስጥ ሁለት የባህር ዳርቻዎች፣ ጎጆ ቤት ውስጥ የሚገኝ ሙዚየም እና ለአዕዋፍት ቅኝት የሚመች ተራራ ይገኛል።

በየዓመቱ መስከረም ላይ ሰባት ቀናት የሚቆይ ፌስቲቫል በደሴቱ ይካሄዳል። በጎ ፍቃደኞች ጊዜያዊ ካፍቴሪያ ይከፍታሉም።

አይል ማርቲን ትረስት የተባለ ማኅበር ደሴቱን በበላይ ጠባቂነት ይዞታል። እአአ በ1999 የተራድኦ ድርጅት የሆነው አይል ማርቲን ትረስት ደሴቱን ያገኘው በስጦታ ነው።

ላለፉት 30 ዓመታት ደሴቱ ነዋሪ አልባ ነበር። አዲሱ ሠራተኛ ከ30 ዓመታት በኋላ በደሴቱ ለመኖር የመጀመሪያ ይሆናል።

ደሴቱን ከፕላስቲክ መገልገያዎች ነጻ ለማድረግ ታቅዷል።

የበላይ ጠባቂ ማኅበሩ ኃላፊ ቤኪ ቶምሰን ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የሚቀጥሩት ሠራተኛ በደሴቱ ውስጥ የሚገኙትን የሕዝብ መጸዳጃዎችና መኖሪያ ቤቶች የማጽዳት፣ እንግዶችን ወደ ደሴቱ የመቀበልና እንግዶቹ የኮሮናቫይረስ መከላከያ መርሆችን እንዲተገብሩ ማስቻል ኃላፊነቱ ነው።

ሥራው በቀን ውስጥ ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ይወስዳል።

ሠራተኛው በነጻ ደሴቱ ውስጥ ከመኖር ባሻገር በሳምንት 150 ዩሮ ይከፈለዋል።

400 ኤከር ስፋት ያለው ደሴት ሌሎችም ደሴቶች በአቅራቢያው ያዋስኑታል።

ከዚህ ቀደም በውስጡ ገዳምና የዱቄት ማምረቻ ነበረው። አሁን ደግሞ የአዕዋፍት ማቆያ ተብሎ ተከልሏል።

ወደ ደሴቱ የሚያቀኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳልፉት ከቤት ውጪ ነው። ይህም ከተፈጥሮ ጋር ለመተሳሰር እድል ይሰጣቸዋል።

በደሴቱ የሞቀ ውሃ የለም። የኤሌክትሪክ ኃይሉም ስልክና ላፕቶፕ ቻርጅ ከማድረግ የዘለለ አቅም የለውም።

ደሴቱን ለመጠበቅ ለወጣው ሥራ የሚያመለክት ሰው ጀልባ መቅዘፍና ሌሎችም በደሴት ለመኖር የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን ማወቅ ይጠበቅበታል።

"ሠራተኛው በደሴቱ መኖር ካስደሰተው የአትክልት እርሻውን መንከባከብና ሌላም ሥራ መሥራት ይችላል። ቦታው ሰላማዊና የተረጋጋ ስለሆነ ይወደዳል። መኪና የለም፤ የመንገድ ዳር ጫጫታ የለም። ለማረፍ የተመቸ ነው" ብለዋል ቤኪ ቶምሰን።