ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይኪ ከኔይማር ጋር የተለያየው ከወሲባዊ ጥቃት ምርመራ ጋር በተያያዘ ነው አለ
የስፖርት አልባሳት አምራቹ ናይኪ ከታዋቂው ብራዚላዊ እግር ኳስ ተጫዋች ኔይማር ጋር መስራት ያቆመው ተጫዋቹ በቀረበበት ወሲባዊ ጥቃት ምርመራ አልተባበበርም በማለቱ እንደሆነ አስታወቀ።
ኔይማር የናይኪ ሠራተኛ ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈፅሟል የተባለው በአውሮፓውያኑ 2016 ሲሆን ለኩባንያው ደግሞ ሪፖርት የተደረገ በ2018 ነው።
ናይኪ ምርመራው እንዳልተጠናቀቀም ገልጿል።
የኔይማር ቃለ አቀባይ በበኩላቸው ደንበኛቸው የተወነጀለበትን ወሲባዊ ጥቃት እንዳልፈፀመና ኔይማር ከናይኪ ጋር ባለፈው ዓመት መስራት ያቆመው ከንግድ ጋር በተገናኘ ምክንያት ነው ብለዋል።
"ኔይማር እንደዚህ አይነት መሰረት ቢስ ውንጀላዎች ሲቀርቡ ራሱን እስከ መጨረሻው ድረስ ይከላከላል። ማስረጃዎች ካሉ ያቅርቡ እስካሁንም ድረስ ምንም አይነት ማስረጃ ማምጣት አልቻሉም" በማለት ቃለ አቀባይዋ ለዋል ስትሪት ጆርናል ተናግረዋል።
ናይኪ ከፍተኛ ስፍራ ከተሰጠው ከኔይማር የስፖንሰር ስምምነት ያቋረጠው በነሐሴ 2020 ነው።
በወቅቱ ኩባንያው ከኔይማር ጋር የነበረውን ስምምነት ለምን እንዳቋረጠ ምክንያት አልሰጠም።
ኩባንያው ባለፈው ሐሙስ ባወጣው መግለጫ "ናይኪ ያለምንም ማስረጃ ዝም ብሎ ውንጀላዎችን ማቅረብ ተገቢ ነው ብሎ አያምንም" ካለ በኋላ አክሎም "ናይኪ ከኔይማር ጋር የነበረውን ግንኙነት ያቋረጠው ከአንድ ሠራተኛ የደረሰንን የሚታመን መረጃ በደረሰን መሰረት ምርመራ እንዲካሄድ ብንጠይቀው እምቢተኝነቱን ስላሳየ ነው" በማለት አስፍሯል።
ጥቃት ተፈፅሞባታል የተባለችው የኩባንያው ሠራተኛ ሪፖርት ያደረገችው በ2018 ሲሆን በመጀመሪያ ላይ ምርመራ እንዲከፈት ፈቃደኛ አልነበረችም።
በምስጢርም እንዲያዝ ፈልጋ ነበር። ከዓመት በኋላ ሠራተኛዋ ምርመራ እንዲደረግ በጠየቀችው መሰረት ኩባንያው ምርመራ መክፈቱን አስታውቋል።
ጥቃቱ ደርሶባታል የተባለችው ግለሰብ ስም ያልተጠቀሰ ሲሆን ኩባንያውም በመግለጫው "የግለሰቧን ማንነት እንዲገለጽ ስለማትፈልግ እሱን እናከብራለን። ምን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታም ውስጥ እንዳለች እንረዳለን" በማለት አትቷል።
ኔይማር በአሁኑ ወቅት ፓሪስ ሴይንት ጀርሜይን ለተባለ የፈረንሳይ ክለብ ይጫወታል።
ከሁለት ዓመት በፊት ውንጀላው ሲቀርብበት አልፈፀምኩም ብሎ የካደ ሲሆን ክሱም ወዲያው ውድቅ ተደርጓል።