በምዕራቡ ዓለም የሥራ አስፈጻሚዎች ደመወዝ ለምን በሚሊዮን ዶላሮች ሆነ?

የፎቶው ባለመብት, Alamy
በአውሮፓና አሜሪካ ለምን ለሥራ አስፈጻሚዎች በሚሊዮን ዶላር ይከፈላል?
ካፒታሊዝም ነው፡፡ ድሆች ይበልጥ ድሀ፣ ሀብታሞች ይበልጥ ሀብታም እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡
ካፒታሊዝም ነው፡፡ ሀብታሞች በጣም ሀብታም፣ ወዝ አደሮች ደግሞ ከድህነት አረንቋ ይወጣሉ፡፡ ቀስ በቀስ፡፡
ሁለቱ አተያዮች ሊያከራክሩ ይችላሉ፡፡ ሁለቱም ግን እውነትነት አላቸው፡፡
የዓለም አዱኛ ከዓለም ሕዝብ 1 እጅ እንኳ በማይሞሉ ጥቂት ሰዎች መያዙ ግን አያከራክርም፡፡
የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ደመወዝ ነው፡፡ የወዝ ደም፤ የላብ ክፍያ፡፡
የሚያልባቸው ሁሉ ለምን ተቀራራቢ ደምወዝ አይከፈላቸውም? የነጭ ባለኮሌታዎች ዋጋ ለምን ይንራል?
ዋናዎቹ ባለጉዳዮቻችን የኩባንያ ባለቤቶች ሳይሆኑ ሥራ አስፈጻሚዎቻቸው ናቸው፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ኩባንያዎች ፈጣሪዎቻቸው ሥራ አስፈጻሚዎቻቸውም ጭምር ናቸው፡፡ እነሱንም እንመለከታለን፡፡
ደመወዝና የፍትሐዊነት ጥያቄ
ይቺ ዓለም ፍትሐዊ ናት? ይህ ጥያቄ እንደመላሹ ነው፡፡
በሚሊዮን ዶላር የሚከፈለው አለቃ ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ አዎንታዊ ነው፡፡ ለላብ አደሩ አሉታዊ ነው፡፡
በ2020 ብዙ ኩባንያዎች የገንዘብ ቀውስ ገጥሟቸዋል፡፡ ብዙዎች ሠራተኞቻቸውን በትነዋል፡፡ ያም ሆኖ ለሥራ አስፈጻሚዎቻቸው በሚሊዮን ዶላሮች ከፍለዋል፤ ይከፍላሉ፡፡
ለምሳሌ የአሜሪካኑን ጎልድማን ሳክስ ባንክ ሥራ አስፈጻሚ ዴቪድ ሰሎሞንን ደመወዝ እንውሰድ፡፡ በዓመት 30 ሚሊዮን ዶላር በአማካይ ወደ ባንክ ደብተሩ ሸርተት ብሎ ይገባለታል፡፡
ዘንድሮ ብቻ ነው 10 ሚሊዮን የተቀነሰበት፡፡ እሱም ከማሌዢያ መንግሥት ጋር በተፈጠረ ምዝበራ የተነሳ ነው፡፡
ድሮ ደመወዝ እንደዚህ አልበረም፡፡ በላብ አደሩና በአሰሪ አለቆች መካከል እንዲህ የሰማይና የምድር ያህል የሚራራቅ ክፍያ ልዩነት አልነበረም፡፡
የሎንዶኑ ‹ሃይ ፔይ ሴንተር› የሠራው አንድ ጥናት የፋይናንሻል ታይምስ ስቶክ ኤክሰቼንጅ (ኤፍቲኤስኢ) ኃላፊዎች በአማካይ 5 ሚሊዮን ዶላር ነው ደመወዛቸው ይላል፡፡
ይህ ማለት ሁሉም ቋሚ ሰራተኞች ከሚያገኙት ድምር መቶ እጥፍ ማለት ነው፡፡
ኢካዶ የድረገጽ ሱፐርማርኬትን እንውሰድ፡፡ ሥራ አስፈጻሚው ቲም ስቴይነር በ2019 ዓ/ም ደመወዙ ስንት ነበር? ማመን ይከብዳል፡፡ 59 ሚሊዮን ዶላር፡፡
አዎ አልተሳሳቱም፡፡ 59 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ደመወዝ ይከፈለዋል፡፡
ይህ ክፍያ ማለት አማካይ የሱፐርማርኬቱ ሰራተኞች በጠቅላላ ተደምሮ 2ሺ 605 ጊዜ እጥፍ ክፍያ ማለት ነው፡፡
በሌላ ቋንቋ ቲም በቀን የሚከፈለው የሌሎቹ የዓመት ደመወዛቸው ተደምሮ በ7 ቢባዛ የሚያገኙት ነው፡፡ እና ይቺ ዓለም ፍትሐዊ ናት?
ለቲም ትሆን ይሆናል፡፡ ካች አፕና የጨው ብልቃጥ ለሚደረድር የኢካዶ ሠራተኛ ግን በፍጹም፡፡
አትላንቲክን እንሻገር፡፡
ዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢኮኖሚክ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት በሠራው ጥናት 350 የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች ሥራ አስፈጻሚዎች የሚያገኙት አማካይ ደመወዝ 21 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
ይህ ጥናት ይፋ የሆነበት ጊዜ ራሱ አስገራሚ ነው፡፡
በሽታ ሰው አይመርጥም ይባላል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ግን ደሃና ጥቁሩ ላይ ነው የበረታው፡፡ ለምን? ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡
አንዱ ላብ አደሩ የጤና መድኅን የለውም፡፡ ሌላው ላብ አደሩ የሚሠራበት ሁኔታ ለተህዋሲው የሚያጋልጥ ነው፡፡ ሌላው ላብ አደሩ ጥሮ ግሮ ሲሠራ ፋታ የለውም፡፡ ራሱን ለመጠበቅ አይችልም፡፡ ሌላው ላብ አደሩ የሚያድረው ባልተመቻቸ ሁኔታና በተጨናነቀ ጭርንቁስ ሰፈር ነው፡፡
የዚህ ሁሉ ምንጭ የክፍያ ማነስ ነው፡፡
ለምሳሌ ‹ወሳኝ ሠራተኞች› እያለ ሚዲያው የሚጠራቸው ለፍቶ አዳሪዎች የሰውን ነፍስ ለማዳን ራሳቸውን የሚያጋልጡ ናቸው፡፡ የጤና ረዳቶችን ይጨምራል፡፡
ሆኖም ሕዝብ እየወጣ ሻማ አበራላቸው እንጂ ክፍያ አልጨመረላቸውም፡፡
ብዙ ሚስኪን ላብ አደሮች ለፍተው ሲያድሩ በዚያው ፍግም ብለው ያልፋሉ፡፡ አኗኗራቸውም አሟሟታቸውም አላማረም፡፡
የካታሊስት ሥርዓት ግን ሊያደርግ የቻለው ደማቅ የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ማሰናዳት ነው፡፡ ሌላም ያደረገው ነገር አለ፡፡ ሚሊዮን ዶላር የሚያገኘው/የምታገኘው ሥራ አስፈጻሚ በሻማ ማብራቱ ሥነ ሥርዓት ላይ የሐዘን ቃል ያሰማሉ፡፡
ትርፋማነት ላይ የተንጠለጠለ ክፍያ
ይህ ለሥራ አስፈጻሚዎች ቁልል ደመወዝ የመክፈሉ ሐሳብና ፖሊሲው በሬገን መንግሥት ጊዜ ነው ይበልጥ እየተዋወቀ የመጣው ይባላል፡፡
በታላቋ ብሪታኒያ ደግሞ ማርጋሬት ታቸር ናቸው የጀመሩት ይላሉ፡፡
ምናልባት የፖለቲካ ፍልስፍናቸው የነጭ ካፒታሊዝም ስለነበር ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ ሁሉም ነገር ወደ ግል ዘርፉ እየሄደ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ለነጻ ገበያ ተላልፎ እየተሰጠ ነበር፡፡
ሬገንም ሆኑ ታቼር የሠራተኛ ማኅበራትን በበጎ አይመለከቱም ነበር፡፡
ለዚህም ይመስላል ሠራተኞች ለክፍያ መሻሻል ሳይታገሉ፣ ቢታገሉም ፍሬ ሳያፈራላቸው እንዲሁ ላብ አደር ሆነው ጉልበታቸው ሲበዘበዝ የኖረው፡፡
"ያንን ዘመን ልብ ብለን ካስተዋልን ክፍያ ሲሻሻል የሁሉም በአንድ ላይ ነበር እንጂ የሥራ አስፈጻሚው ለብቻ ተነጥሎ አይታይም ነበር" ይላሉ ሳንዲ ፔፐር፡፡ ሳንዲ በሎንዶን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ የክፍያ ጉዳዮች ተመራማሪ ናቸው፡፡
ሳንዲ ለምን በየዘመኑ የተራ ሠራተኞችና የሥራ አስፈጻሚዎች ክፍያ እየተንቦረቀቀ መጣ በሚለው ላይ ጥናት አድርገዋል፡፡
ቀድሞ አለቃና ተራው ሠራተኛ በክፍያ ጭማሪ ወቅት በእኩል ይታይ የነበረው አሠራር እየፈረሰ የመጣው የሥራ አስፈጻሚዎች ክፍያ ከሽርክና ዋጋ እና ውጤት ተኮር አበሎች ጋር እየተሳሰረ መምጣቱን ተከትሎ ነው፡ ይላሉ ሚስተር ሳንዲ፡፡
ትርፍን ብቻ የሚያሳድደው ኒዎ ሊበራሊዝም ይህን አሠራር እያበረታታው መጣ፡፡
ከ2000 ዓ/ም ጀምሮ የተወሰደ የኤፍቲኤስኢ100 ዳታ እንደሚያሳያው የሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ በየዓመቱ በአማካይ 3 ከመቶ ሲሆን የሥራ አስፈጻሚዎች ግን በ10 ከመቶ ይመነደጋል፤ በየዓመቱ፡፡
አሁን ባለው አሰራር የሥራ አስፈጻሚዎችን ክፍያ የሚወስነው የኩባንያዎች ዓመታዊ የትርፍ አፈጻጸም እየሆነ መጥቷል፡፡
ምክንያቱም ሥራ አስፈጻሚዎች ለኩባንያዎች ማበብና መክሰም ወሳኞች እየሆኑ መምጣታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ይህ ሁኔታ ከመደበኛ የደመወዝ ምጣኔ በተጨማሪ ሥራ አስፈጻሚዎች ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንዲንበሸበሹ አድርጓቸዋል፡፡
ከነዚህም መካከል በኩባንያው ውስጥ ድርሻ እንዲኖራቸው በማድረግ የባለቤትነት ስሜት እንዲያድርባቸው ማስቻል፤ ኩባንያው ትርፋማ ሲሆን ደግሞ በተገኘው ትርፍ ልክ አበል መስጠትን ያካትታል፡፡
ለአብነት ቅድም ባነሳነው የኢካዶ የድረ ገጽ ሱፐርማርኬት ምሳሌ ሥራ አስፈጻሚው ስቴይነር በ2019 ከተከፈላቸው ዓመታዊ ደመወዝ ውስጥ 54 ሚሊዮን ፓውንድ ጉርሻ ይገኝበታል፡፡
ይህም የኩባንያውን የ5 ዓመት የእድገትና ትርፍ እቅድ በማሳካታቸው ያገኙት ነው፡፡
ብዙውን ጊዜ ኩባንያዎች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም የሚወስንላቸው በዓመት አንድ ጊዜ በሚሰበሰብ ቦርድ ነው፡፡
የቦርድ አባላት ደግሞ ከሌሎች ኩባንያዎች የተውጣጡ ሥራ አስፈጻሚዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ይህ በእንዲህ ሳለ ብዙዎቹ የብሪታኒያ ቢዝነሶች በግለሰቦች ባለቤትነት መሆናቸው በአያሌው ቀንሷል፡፡
የትልልቅ ሼር ባለቤቶች ጡንቻ እየፈረጠመ ነው የመጣው፡፡ እነሱ ደግሞ የስቶክ ዋጋ በፍጥነት እንዲጨምርላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ ለሥራ አስፈጻሚዎች ወፍራም ደመወዝ ይከፍላሉ፡፡
የቦርድ አባላት ደግሞ የሼር ባለቤቶችን ለማስደሰት የሥራ አስፈጻሚን ደመወዝ ከፍ ያደርጋሉ፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ጥቅማ ጥቅም የሚሰላው ከተመሳሳይ ኩባንያዎች ጋር በማወዳደር ነው፡፡ እነሱ በሌላ ኩባንያዎች ሥራ አስፈጻሚ ስለሆኑ የሌላውን ሲያሻሽሉ የነሱም እንደሚሻሳል ይረዳሉ፡፡ ስለዚህ ወፍራሙን ደመወዝና ቁልሉን አበል ያጸድቁታል፡፡
አንዳንድ ጊዜ የቦርድ አባላት ከሠራተኞችም ይወከላል፡፡
ሠራተኞች ትልቁን አለቃ ማስቀየም አይፈልጉም፡፡ ነገ ሊያባርራቸው ይችላል፡፡ ወይም በትርፍ ላይ ያለን ኩባንያ ጥሎ ሄዶ ኮርፖሬሽኑን ለሌላ ኪሳራ ሊያጋልጠው ይችላል፡፡ ኩባንያው ከሰረ ማለት የሥራ ዋስትና ታጣ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የክፍያ ጭማሪን በምንም መልኩ ለመቃወም አይደፍሩም፡፡
ሥራ አስፈጻሚዎች ግን ያን ያህል ልዩ ፍጡር ናቸው?
ምንም እንኳ ለሥራ አስፈጻሚዎች የሚከፈለው ረብጣ ዶላር ልክ ነው አይደለም በሚለው ላይ ሰፊ ክርክር ቢኖርም የነጻ ገበያ አቀንቃኝ የሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ግን አስፈጻሚዎች ለኩባንያ የሚያመጡት ገቢ አጥጋቢ እስከሆነ ድረስ የሚያጠግብ ደመወዝ መከፈሉ ምንድነው ችግሩ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
ነገሩ ሁሉ ገበያ መር ነው፡፡ አንድ ኩባንያ በኪሳራ እየሰመጠ ለአለቆች ያን ያህል ሊከፍል አይችልም፡፡ ገበያ መር ስንል የቁስ ዋጋን ብቻ ሳይሆን የወዝአደር ዋጋም ማለታችን ነው ይላሉ፡፡
"ሥራ አስፈጻሚዎች ቁልፍ የስኬት ሞተሮች ናቸው፡፡" ይላሉ በአዳም ስሚዝ ኢንስቲትዩት የኒዮሊበራል ባለሙያዎች ስብስብ (ቲንክታንክ) ፕሮግራም ኃላፊ ዳኒኤል ፕራዮር፡፡
"ግልጽ ነው እኮ፤ አንድን ኩባንያ አትራፊ ማድረግ የሚያስችል የአስተዳደር ጥበብ፣ የዕውቀት ስንቅና ብልሀት ያላቸው ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡ በገበያው እንዲህ ዓይነት ላቅ ያለ የአመራር ክህሎት ሁሉም ሰው የለውም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጥቂት ሰዎች ላይ ገበያው ይራኮታል፡፡ ክፍያቸው ጣሪያ የሚነካውም ለዚሁ ነው" ይላሉ፡፡
ዴቪድ ቦልቾፈር ግን በዚህ አይስማሙም፡፡
"ማነው የአመራር ክህሎት ያላቸው ሰዎች ጥቂት ናቸው ያለው ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ይሄ ማጭበርበር ነው፡፡"
ሚስተር ዳንኤል ክፍያው ተገቢ ነው የሚሉት የአፕሉን ስቲቭ ጆብስ፣ የአማዞኑን ጄፍ ቤዞስ፣ የተስላና የስፔስኤክስ ፈጣሪን ኤሎን መስክንና የመሳሰሉትን እጅግ የነጠረ ክህሎት በማንሳት ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች አዲስ ነገር ፈጥረው የገበያና የቴክኖሎጂ አብዮት ያመጡ ሰዎች ናቸው፡፡
"መደበኛ ሥራ አስፈጻሚዎች ግን እንደነ ኤሎን መስክ ያሉት አይደሉም" ይላሉ ዴቪድ ቦልቾፈር፡፡
እነዚህ መደበኛ ሥራ አስፈጻሚዎች ሚናቸውም ክፍያቸውም የተጋነነ ነው ብለው የሚከራከሩትም ለዚሁ ነው፡፡
አንድ ኩባንያ በሥራ አስፈጻሚው ብርታትና ምጥቀት ብቻ አይደለም ትርፋማ የሚሆነው የሚሉት ሚስተር ዴቪድ ፔይ ቼክ በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ይህን ጉዳይ በዝርዝር ጽፈውታል፡፡
አንዳንድ ዘርፎች በተለያዩ ምክንያቶች አትራፊነታቸው ይቀጥላል፤ የትኛውም ተመሳሳይ አቅም ያለው ሰው ቢመራቸው፡፡
የቴሌኮም ዘርፎችን ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ ወይም ቀድሞውኑም ጥሩ መሠረት ላይ የተገነቡ ቢዝነሶች፡፡ በዚህ ረገድ ሥራ አስፈጻሚዎች ምንም ቦታ ላይኖራቸው ይችላል፡፡ ምናልባት የሠራተኞች ትጋት ይሆናል የትርፍማነቱ ምንጭ፡፡ ሆኖም አለቆች የሚበሉት ደመወዝ የትየሌሌ ነው፡፡
"በኮርፖሬሽኖች የሥራ አስፈጻሚዎች ሚና ብዙውን ጊዜ ይጋነናል፡፡ ይህ ሆን ተብሎ የሚደረግ ማጭበርበሪያ ነው፡፡" ይላሉ ዴቪድ ቦልቸር፡፡
ቦልቸር ሌላም ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡
ለምሳሌ የ2008 የፋይናንስ ቀውስ ጊዜ ባንኮች በኪሳራ ሲንኮታኮቱ ሥራ አስፈጻሚዎቻቸው ግን ሚሊዮን ዶላሮችን ታቅፈው ነው የሄዱት፡፡ ይህ ነገር በጊዜው ብዙዎችን አቁስሎ ነገሩ ላይ ጥያቄም መነሳት ጀምሮ ነበር፡፡
"ክፍያ አስፈጻሚዎች ባስገኙት የስኬት መጠን ነው ከተባለ የነዚህ ባንኮች ሥራ አስፈጻሚዎች ለምን ከኪሳ በኋላም ወፍራም ደመወዝ እየተከፈላቸው ቆዩ?" ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ መልሱን ራሳቸው ሲመልሱም የጥቅም ትስስር ስላለ ነው ይላሉ፡፡ የጥቅም ትስስሩ በቦርድ አባላት፣ በሥራ አስፈጻሚዎችና በሽርክና ባለቤቶች መካከል ነው፡፡
ተራው ሠራተኛ ደመወዙ ለምን ያሽቆለቁላል?
የሥራ አስፈጻሚዎች ደመወዝ ሲመነደግ የተራ ሠራተኛው ደመወዝ ቁልቁለቱን ተያይዞታል፡፡ ለምሳሌ በዚህ ወረርሽኝ የወሳኝ ሰራተኞች ደመወዝ ማነሱ ብቻ ሳይሆን እሱንም ለማግኘት ሕይወታቸው ላይ ለመቆመር ይገደዳሉ፡፡
ይህ የተራ ሠራተኞች ደመወዝ ማሽቆልቆል ብዙዎችን ደም እያፈላ ነው፡፡ ለምሳሌ በሺህ የሚቆጠሩ የብሪቲሽ ጋስ ኩባንያ ሰራተኞች የ5 ቀን የሥራ ማቆም አድማ አድርገው ነበር፡፡
ምክንያታቸው ደግሞ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የሠራተኛ ቅነሳ መደረጉ ነው፡፡ ብዙ ሠራተኞች በጥቂት መብቶች ብቻ ተወስነው በአስቸጋሪ ሁኔታ እንዲሰሩ መገደዳቸው ነው፡፡
ውጥረቱ ይበልጥ የተካረረው ደግሞ ከ2018 ጀምሮ ብሪቲሽ ጋስን በባለቤትነት የያዘው ሴንትሪካ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ የ44 ከመቶ ጭማሪ ማግኘታቸውን ተከትሎ ነው፡፡ ዓመታዊ ደመወዛቸው 2 ሚሊዮን ተኩል ፓውንድ ያልፋል፡፡
"ይህ ስግብግብነት ነው" ይላል የ32 ዓመቱ የብሪቲሽ ጋስ ሰራተኛ ጆን፡፡ ይህ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንኳ የማይከፈላቸው ደመወዝ መጠን ነው፡፡ እንዴት ነው ሰራተኛን እየቀነሰ ያለ ኩባንያ ለሥራ አስፈጻሚው ይህን ያህል ፓውንድ የሚከፍለው? በጭራሽ ስሜት አይሰጥም፡፡
አንዳንድ መልካም ሥራ አስፈጻሚዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የቦይንግ፣ የማሪዮት ኢንተርናሽናል የፒደብሊውሲ ሥራ አስፈጻሚዎች ሰራተኛ እንዳይቀነስ ሲሉ ደመወዛቸውን ጭማሪ ይቅርብን ያሉ ናቸው፡፡
አንዳንዶች ይህን ድርጊታቸውን ለታይታ የተደረገ እንጂ መሰረታዊ ለውጥ የማያመጣ ነው ሲሉ ይተቹታል፡፡
መጪው ጊዜ አስፈሪ ነው፡፡ ለተራ ሰራተኛ፣ ለላብ አደሩ፣ ድምጹ ለማይሰማው፣ ላቡ ለሚንቆረቆረው ብዙኃን በተለይ መጪው ዘመን ቀበቶ ጠበቅ የሚደረግበት ነው፡፡
ምክንያቱም ኩባንያዎች ገቢ ቀንሷል፡፡ ከቴክ ኩባንያዎች ውጭ ያለው ዘርፍ በወረርሽኙ ድባቅ ተመቷል፡፡ የአርተፊሻል ልህቀትና ሌሎች ማሽኖች የጉልበት ሥራን ዋጋ እያሳጡት ነው፡፡ ኢንተርኔት ንግድ የሰራተኛን አስፈላጊነት እምብዛምም አድርጎታል፡፡ ፋይናንስ ኢንዱስትሪዎች በእንብርክክ እየሄዱ ነው፡፡ የሰራተኛ ማኅበራት እየተዳከሙ ሄደዋል፡፡
ስለዚህ መጪው ጊዜ ሚሊየነሮች ቢሊየነሮች የሚሆኑበት፣ ላብ አደሮች ይበልጥ ላባቸው በከንቱ የሚፈስበት እንደሆነ የዓለም ምጣኔ ሀብትን በቅርብ የሚከታተሉ አዋቂዎች ትንቢት ነው፡፡
የዓለም ሀብት በጥቂቶች እጅ ይቀፈደዳል፡፡ ቢሊዮኖች ግን በቃ ቁጥር ናቸው፡፡ ተወልደው፣ ኖረው፣ ጥረው ግረው፣ የሚሞቱ፡፡












