አፕል በሦስት ወራት ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሽያጭ አካሄደ

አፕል ኩባንያት በሦስት ወራት ብቻ ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሽያጭ አካሄደ።

በፈረንጆቹ የገና በዓል መዳረሻ በርካታ ደንበኞቼ ቅርንጫፎቼን አጥለቅልቀውት ነበር፡፡ ከስልክ፣ ከላፕቶፕና ሌሎች ቁሳቁሶች ሽያጭ የሰበሰብኩት 111 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ብሏል አፕል።

ይህ ሽያጭ የ2020 ዓ/ም የመጨረሻዎቹ 3 ወራትን ብቻ የሚሸፍን ነው፡፡

የቴክኖሎጂ ገበያን ሥራዬ ብለው የሚከታተሉ ባለሙያዎች ነገሩ የኮቪድ ወረርሽኝ ያመጣው ዕድል ነው ይላሉ። ምክንያቱም ወረርሽኙ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ስላስከተለ በርካታ ሰዎች የቴክኖሎጂ ምርቶችን እንዲገዙ ምክንያት ሆኗቸዋል።

አፕል በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም አንድ ቢሊዮን ተኩል ምርቶቼ በሰዎች እጅ ላይ ይገኛሉ ይላል፡፡ ይህ አሐዝ በአገልግሎት ላይ ያሉትን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ ከነዚህ ውስጥ 1 ቢሊዮን የሚሆኑት አይፎን ስልኮች ናቸው፡፡

የአፕል ገበያ የደራበት ሌላው ምክንያት የአይፎን-12 ስልክ ገበያ ላይ መዋሉ ነው፡፡ ይህም በርካታ የአይፎን ታማኝ ደንበኞች የቀድሞ ስልካቸውን ወደ አዲሱ ስልክ ለመቀየር ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ መደብሮችን አጨናንቀው ታይተዋል፡፡

ኩባንያው እንዳለው የተህዋሲው መነሻ በሆነችው አገር ቻይና ገበያው ይበልጥ ደምቆልኝ ነበር ብሏል፡፡ በተለይም የ5ጂ ቴክኖሎጂ ጋር መግባባት የሚችሉ ስልኮች በቻይና መፈለጋቸው ገበያዬን ከጠበቅኩት በላይ አድምቆልኛል ብሏል፤ አፕል፡፡

በመቶኛ ሲሰላ ሆንግ ኮንግና ታይዋንን የሚያካልለው መላው ቻይና 57 ከመቶ፣ የአውሮጳ ገበያ 17 ከመቶ እንዲሁም የአሜሪካ ገበያ 11 ከመቶ ሆኗል፡፡

የአፕል ታማኝ ደንበኞች አዲሱ ምርት ከአዳዲስ የቴሌኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂዎች ጋር መጣጣማቸው በግዢ ላይ እንዳያቅማማ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡

የኮቪድ ወረርሽኝ ለበርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸዋል ተብሏል፡፡

የአፕል ከመቶ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሽያጭ ማስመዝገቡ እንዳለ ሆኖ ፌስቡክና ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም በትርፍ የተንበሸበሹበት ዓመት ሆኖ አልፏል፡፡

ወረርሽኙ የዓለምን ሕዝብ ቤቱ እንዲቀመጥ ሲያደርገው በርካታ ሰዎች ግብይትም ሆነ ሌሎች ሥራዎችን ለመከወን የሚረዷቸው መሣሪያዎች ላይ ያተኩራሉ፡፡ ግብይቱም በበይነ መረብ የሚከወን ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደማመር የቴክ ኩባንያዎች ገቢ እንዲመነደግ ያደርጋል፡፡