ጀርመን አዛውንት ዜጎቼን አስትራዜኔካ የኮቪድ ክትባትን አልከትብም አለች

የጀርመን የክትባት ኮሚቴ አስትራዜኔካ ክትባት መሰጠት ያለበት ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በታች ለሆኑት ብቻ ነው ሲል ውሳኔ አሳለፈ።

ኮሚቴው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በአዛውንቶች ላይ ክትባቱ ያስገኘው ውጤትን በተመለከተ በቂና የማያወላዳ ሳይንሳዊ ማስረጃ ባለመገኘቱ ነው።

የአውሮጳ መድኃኒት ኤጀንሲ ዛሬ አርብ አስትራዜኔካ ክትባት ዕድሜያቸው ለገፉ ሰዎች ይሰጥ ወይስ አይሰጥ በሚለው ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

ታላቋ ብሪታኒያ ይህን ክትባት በሁሉም ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ዜጎቿ እየሰጠች ትገኛለች። የጤና ባለሙያዎችም ደኀንነቱ የሚያሰጋ አይደለም፤ ከፍ ያለ መከላከል አቅምም አለው ሲሉ ይናገራሉ።

ጀርመን ግን ይህን አሳማኝ ሆኖ አላገኘችውም።

የአውሮጳ ኅብረትና አስትራዜኔካ ኩባንያ ከሰሞኑ በምርት አቅርቦት ማነስ ምክንያት ሲነታረኩ ነው የከረሙት። ይህ የጀርመን ዜና የመጣውም ይህ አለመግባባት ባልተቋጨበት ወቅት ነው።

አስትራዜኔካ እንደሚለው በአውሮጳ ያሉ መድኃኒቱን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ያሉባቸው ችግሮች ካልተቀረፉ ክትባቱን ለአውሮጳ በተባለው ጊዜ ለማድረስ እንደሚቸገር ይናገራል።

ነገር ግን የአውሮጳ ኅብረት አስትራዜኔካ ውል ገብቷል፤ ውሉን ማክበር አለበት፤ በታላቋ ብሪታኒያ ያለውን ክምችት ለአውሮጳ ኅብረት ሊሰጥ ይገባል ይላል።

ይህን ማድረግ ካልቻለ ወደ ሕግ እንደሚሄድም ኅብረቱ አስታውቋል።

አስትራዜኒካ ብቻም ሳይሆን ፋይዘር እና ባዮንቴክም በተመሳሳይ ለ27ቱ የአውሮጳ ኅብረት አባል አገራት ክትባት በወቅቱ ማድረስ እንደማይችል አስታውቋል።

የጀርመን መንግሥትን በክትባቶች ዙርያ የሚያማክረው የባለሙያዎች ኮሚቴ እንደወሰነው አስትራዜኔካ በአዛውንቶች ዘንድ የሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳትን በተመለከተ አስተማማኝ ሳይንሳዊ መረጃዎች እስኪገኙ ድረስ ጀርመን ክትባቱን መስጠት ያለባት ከ18 እስከ 64 ዓመት ለሆናቸው ዜጎች ብቻ ነው።

ነገር ግን የታላቋ ብሪታኒያ የክትባት ዘመቻ መሪ ዶ/ር ሜሪ ራምሴይ በዚህ አይስማሙም። እሳቸው እንደሚሉት አስትራዜኔካም ሆነ ፋይዘር ዕድሜያቸው ለገፉ ሰዎች መስጠቱ ጉዳት አላሳየም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የጀርመን ኮሚቴ ያስተላለፈው ውሳኔ እንደማይረብሻቸውና አስትራዜኒካን ለሁሉም ዜጎች በስፋት ማደላቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።