ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቀዳማይት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ያስገነቧቸው 18 ትምህርት ቤቶች
የቀዳማይት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት በመላው አገሪቱ በ300 ሚሊዮን ብር 18 ትምህርት ቤቶችን ሰርቶ መጨረሱን የጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሉቀን ፋንታ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከእነዚህ ግንባታቸው ከተጠናቀቁ ትምህርት ቤቶች መካከል 13 ትምህርት ቤቶች ተመርቀው ለአካባቢዎቹ አስተዳዳሪዎች የተሰጡ ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ጽህፈት ቤቱ አምስት ትምህርት ቤቶችን እንደሚያስመርቅ ኃላፊው ተናግረዋል።
እነዚህ ግንባታቸው አልቆ የተመረቁም ሆነ በቅርቡ የሚመረቁ ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መሆናቸውን አቶ ሙሉቀን አክለው ተናግረዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው ከመደመር መፅሀፍ ገቢ ለሚሰሩ ትምህርት ቤቶች መሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ መጀመራቸውንም አቶ ሙሉቀን አስረድተዋል።
ቀዳማይት እመቤት ያስገነቧቸው የመጀመሪያዎቹ አራት ትምህርት ቤቶች በ2011 ዓ.ም ጽህፈት ቤቱን እንደተረከቡ ግንባታ መጀመሩን ያስታወሱት አቶ ሙሉቀን፣ ቀሪዎቹ ግን 2012 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ግንባታቸው ተጀምሮ መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።
ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸዉ ሚያዚያ 3፣ 2011 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታቸው የተጀመሩት ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ከመስከረም 2012 ጀምሮ ትምህርት መስጠት ጀምሯል።
አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች ከስድስት ወር እስከ ስምንት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ግንባታቸው መጠናቀቁንም አቶ ሙሉቀን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የቦታ ርቀታቸው አመቺ ያልነበሩ ፕሮጀክቶች ብቻ አንድ አመት መውሰዳቸውን ጨምረው ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የቀዳማይ እመቤት ጽህፈት ቤት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለ300 ማየት ለተሳናቸው በአዳሪነት የሚያገለግል ትምህርት ቤት እያስገነባ መሆኑን አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል።
ለእነዚህ ትምህርት ቤቶች የግንባታ ወጪ የወጣውን ገንዘብ በአጠቃላይ ቀዳማይት እመቤት በባህር ማዶ ካሉ ወዳጆቻቸው በስጦታ ማግኘታቸውን ኃላፊው ያስረዳሉ።
ትምህርት ቤት ግንባታ ለምን?
ቀዳማይት እመቤት ጽህፈት ቤቱን አንደተረከቡ ቅድሚያ ከሰጧቸው ጉዳዮች መካከል የትምህርት ቤቶችን ተደራሽነትንና ጥራት ማሻሻል መሆኑን ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።
አቶ ሙሉቀን ትምህርት ቤቶቹ በመላ አገሪቱ የሚገነቡ መሆናቸውን አስታውሰው በመጀመሪያው ዙር እቅድ 20 ትምህርት ቤቶችን ለመሥራት ታቅዶ እነደነበር አስታውሰዋል።
ከዚህ በፊት በቀዳማይት እመቤት ቢሮ ሥር የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ነበር ያሉት ኃላፊው ቀዳማይ እመቤት ዝናሽ በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውረው ትምህርት ቤቶችን በጎበኙበት ወቅት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በአቅራቢያቸው ባለመኖሩ ምክንያት ትምህርታቸውን ከስምንተኛ ክፍል የሚያቋርጡ በርካታ ተማሪዎች መኖራቸውን ማስተዋላቸውን ገልፀዋል።
በመላ አገሪቱ በብዛት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን የሚያስታውሱት አቶ ሙሉቀን ተማሪዎች እስከ ስምንተኛ ድረስ ከተማሩ በኋላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመቀጠል በአቅራቢያ ወዳለ ከተማ መሄድ አስገዳጅ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ይህም የምጣኔ ኃብት ጫና አለው ያሉት ኃላፊው "ልጁን ትምህርት ቤት ልኮ ማስተማር የማይችል ወላጅ እንዲያቋርጥ ይገደዳል" ሲሉ ያስረዳሉ።
ሌላው ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት ነው ያሉት አቶ ሙሉቀን ከቤተሰቦቻቸው ርቀው በሚሄዱበት ወቅት ለጥቃት የመጋለጥ እድላቸው ሰፊ ነው ብለዋል።
እነዚህን ሁለት ችግሮች ለማስቀረት በርካታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ባሉባቸው እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሌሉባቸው አካባቢዎች ትምህርት ቤቶቹ እንዲገነቡ መደረጉን ጨምረው አስረድተዋል።
ትምህርት ቤቶቹ የተገነቡት በመላ አገሪቱ ነው ያሉት አቶ ሙሉቀን፣ በአማራ እና ኦሮሚያ በእያንዳንዳቸው አራት ትምህርት ቤቶች፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ፣ ጌዲኦ፣ ሻኪሶ ሶስት ትምህርት ቤቶች፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳና መተከል ሁለት ትምህርት ቤት፣ ሶማሌ ክልል በጅጅጋ ከተማ ሁለት ትምህርት ቤቶች፣ አፋር አንድ፣ ጋምቤላ አንድ፣ ትግራይ በሽሬ ከተማ አንድ ትምህርት ቤት ተገንብተዋል።
በ2012 ዓ.ም ተጠናቅቀው ለአካባቢው አስተዳደር ርክክብ የተደረገባቸው አራት ትምህርት ቤቶች 26 የመመማሪያ ክፍሎች ያላቸው እና እያንዳንዳቸው ወደ 20 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ሲሆኑ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት በፊት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
እነዚህ ትምህርት ቤቶች በአንድ ፈረቃ ብቻ 1ሺህ 300 ተማሪዎችን ማስተናገድ ይችላሉ ተብሏል።
በትምህርት ቤቶቹ አስፈላጊዎቹን ቁሳቁሶች በማሟላት፣ ለተማሪዎቹም የደንብ ልብስ በማቅረብ ስራ መጀመራቸውን ያስታውሳሉ።
ከእነዚህ አራት ትምህርት ቤቶች ውጪ ያሉት ደግሞ እያንዳንዳቸው 18 የመማሪያ ክፍሎች ሲኖራቸው፣ እያንዳንዳቸው በ13.8 ሚሊየን ብር መገንባታቸውንና አንዱ ትምህርት ብቻ በአንድ ፈረቃ 900 ተማሪዎችን እንሚይዝ ኃላፊው ጠቁመዋል።
በሁሉም ትምህርት ቤቶች የአስተዳደር ቢሮዎች፣ ቤተመጻህፍትና ቤተሙከራ ደረጃቸውን ተጠብቀው መሰራታቸውንም አክለዋል።
በአጠቃላይ እነዚህን ትምህርት ቤት ለመገንባት ብቻ 300 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።
ምዕራፍ ሁለት ግንባታ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የመደመር መጽሐፍ ሽያጭን ለቀዳማይ እመቤት ጽህፈት ቤት ባስረከቡበት ወቅት ገንዘቡ መጽሐፉ ተሸጦ ገቢው ለተሰበሰበበት ክልል ይዋል ባሉት መሰረት አምስት ትምህርት ቤቶች በኦሮሚያና በደቡብ ክልል እንደሚገነባ አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከ መደመር መፅሀፍ ሽያጭ የተገኘዉን 110,671,025.72 ብር ለትምህርት ቤቶች ግንባታ ይውል ዘንድ ለቀዳማይት እመቤት ፅህፈት ቤት ማበርከታቸው ይታወሳል።
በመሆኑም ክልሎች መጽሀፉን ሽጠዉ ካስገቡት ገንዘብ ትምህርት ቤቶቹ እንደሚገነቡ ቃል በተገባላቸዉ መሰረት በኦሮሚያ በምእራብ አርሲ ዞን ሲራሮ ወረዳ ሮጲ ከተማ ለሚገነባዉ ትምህርት ቤት ቀዳማይ እመበት ዝናሽ የመጀመሪያው የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።
የቀዳማይት እመቤት ጽህፈት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ከመገንባት ባለፈ የሴቶችን የምጣኔ ኃብት አቅም ማጎልበት ላይ እንደሚሰራም አክለው ገልፀዋል።
በዚህ ፕሮጀክት በባህር ዳር ከተማ በወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ላይ እንደሚሰራ የገለፁት አቶ ሙሉቀን፣ 695 ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለአይነ ስውራን የትምህርት ቁሳቁስ በማቅረብ፣ ለአካል ጉዳተኞች ዊልቸር ድጋፍ በማድረግ፣ ጽህፈት ቤቱ ይሳተፋል ብለዋል።