ኖቫቫክስ የተሰኘ አዲስ የኮቪድ ክትባት ተገኘ

በብሪታኒያ በሙከራ ላይ የነበረው ኖቫቫክስ ክትባት ስኬታማነቱ ተረጋገጠ። ክትባቱ በሦስተኛ ደረጃ የሙከራ ሂደት ይበል የሚያሰኝ ውጤት ተገኝቶበታል።

ይህ ክትባት በበርካታ ሰዎች ላይ ተሞክሮ 89.3 በመቶ ፈዋሽነቱ በመረጋገጡ ትልቅ የምሥራች ሆኗል።

ይበልጥ አስደሳች የሆነው ደግሞ ይህ ክትባት አዲስ ዝርያ ነው ለተባለው የኮቪድ ዓይነትም አይበገሬነቱን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ማረጋገጥ መቻሉ ነው።

የታላቋ ብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የምሥራቹን በደስታ ተቀብለውታል። የአገሪቱ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንም አሁን ክትባቱን ወስዶ በመመርመር የመጨረሻ ፍቃድ መስጠት ይችላል ብለዋል።

ታላቋ ብሪታኒያ ይህን በሙከራ ላይ የነበረን ክትባት 60 ሚሊዮን ጠብታዎችን ቀደም ብላ አዝዛለች። አሁን በእንግሊዝ በሚገኘው ፋብሪካ ወደ ምርት ሥራ ለመግባት በመጨረሻ ዝግጅት ላይ ነው ይገኛል።

60 ሚሊዮን ጠብታዎች ምርት በዚህ የፈረንጆች ዓመት አጋማሽ ለሕዝብ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ በኋላ የሚቀረው የመጨረሻ ሥራ የብሪታኒያ የመድኃኒትና የጤና ምርቶች ቁጥጥር ኤጀንሲ ክትባቱን በይፋ አገልግሎት ላይ እንዲውል ፈቃድ የመስጠት ሒደት ነው።

ታላቋ ብሪታኒያ እስከ አሁን ሦስት የኮቪድ ክትባቶችን ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እንዲውሉ ፈቅዳለች።

እነዚህም የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲና አስትራዜኔካ ያመረቱትና በአጭሩ አስትራዜኔካ ተብሎ የሚጠራው አንዱ ሲሆን የፋይዘርና ባዮንቴክ ሁለተኛው እንዲሁም ሞደርና ሦስተኛው ነው።

የኖቫቫክስ ክትባት በኤጀንሲው በይፋ ፍቃድ ሲያገኝ አራተኛው የኮቪድ ክትባት ሆኖ ይመዘገባል።

ኖቫቫክስ በዚህ የመጨረሻ ምዕራፍ ሙከራው 15ሺ ሰዎችን ያሳተፈ ሲሆን ኮቪድን በመከላከል ረገድ 89.3% ውጤት አስመዝግቧል። ሙከራ የተደረገባቸው 15ሺ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 84 ነው። ከእነሱ ውስጥ ደግሞ 27 እጅ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ65 በላይ ነበር።

የደቡብ አፍሪካ ዘርያ እየተባለ የሚጠራውና በገዳይነቱም በተዛማችነቱም የሚፈራው የኮቪድ ዝርያን በመከላከል ረገድ ኖቫቫክስ 60 እጅ ተከላካይ ሆኖ መገኘቱም ተነግሯል። ይህም ኤች አይ ቪ በሌለባቸው ሰዎች ላይ የተገኘ ውጤት ነው።

የኖቫቫክስ ኃላፊ ስታን ኤሪክ ዜናው እንደጠበቅነው አስደሳች ነው፤ በደቡብ አፍሪካው ዝርያ የተገኘው ውጤት ደግሞ ብዙ ሰው ከጠበቀው በላይ ነው ብለዋል።

ሚስተር ኤሪክ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህን ክትባት የማምረቱ ሥራ በመጋቢትና ሚያዝያ ወር ይጀምራል ብለዋል። ምርቱን በመድኃኒትና በጤና ምርቶች ቁጥጥር ባለሥልጣን ክትባቱ መጽደቁን ተከትሎ ወዲያውኑ የሚጀመር ነው ብለዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ማት ሐንኩክ የአገሪቱ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት (ኤን ኤች ኤስ) ለዚህ ክትባት መጀመር በተጠንቀቅ ላይ ነው ብለዋል፤

ሐንኮክ 'ይህ መልካም ዜና ነው፤ ለክትባት ዘመቻው ትልቅ አቅም ይፈጥራል' ብለዋል።

የጤና ሚኒስትሩ ኖቫቫክስን ላገኙ ሳይንቲስቶች ያላቸውን ክብር ገልጠውም አመስግነዋቸዋል። በክትባቱ ሙከራ በበጎ ፈቃድ ለተሳተፉትም ትልቅ ክብር አለኝ ብለዋል።

ታላቋ ብሪታኒያ በተህዋሲው የሞቱባት ዜጎች ቁጥር ከመቶ ሺህ በላይ ነው። ሆኖም በከፍተኛ ፍጥነት ለዜጎቿ ክትባት በመስጠት ላይ ትገኛለች።