ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የግዙፉ ጎልድማን ሳክስ ባንክ ሥራ አስፈጻሚ ከደመወዛቸው 10 ሚሊዮን ዶላር ተቀነሰ
ከዓለማችን ግዙፍ ባንኮች አንዱ የሆነው ጎልድማን ሳክስ የሥራ አስፈጻሚውን ደመወዝ በ10 ሚሊዮን ዶላር ቀንሷል።
ዴቪድ ሶሎሞን ደመወዙ የተቆረጠባቸው ባንኩ ባለፉት ዓመታት ከገጠመው ምዝበራና ማጭበርበር ጋር የተያያዘ ነው።
ሆኖም እሳቸው በዚህ 'ታላቅ ማጭበርበር' የሉበትም ተብሎ ተመስክሮላቸዋል። እሳቸው በምዝበራው እጃቸውን ባያስገቡም ባንኩ የከፍተኛ ኃላፊዎችን ደመወዝ ስለቀነሰ ነው የሳቸውንም ለመቀነስ የተገደደው ተብሏል።
ከደመወዛቸው 10 ሚሊዮን ዶላር ባይቀነስ ኖሮ ዴቪድ ሶሎሞን ክፍያቸው 27 ሚሊዮን ዶላር ይደርስ ነበር።
ይህ በባንኩ ታሪክ 'ታላቁ ማጭበርበር' እየተባለ የሚጠራው የገንዘብ ምዝበራ የተካሄደው ከማሌዢያ መንግሥት ጋር ሲሆን ማሊዢያ 1ኤምዲቢ የሚባል ሐሰተኛ የኢንቨስትመንት ፈንድ በማቋቋም ባንኩ ቦንዶችን እንዲሸጥ ከተደረገ በኋላ ገንዘቡ እንደተዘረፈ ተደርሶበታል።
ይህ የሆነው በፈረንጆቹ 2012 ቢሆንም ምርመራው ዛሬም ድረስ አልተጠናቀቀም።
የማሊዢያ መንግሥት ኢንቨስትመንት ፈንድ ከታላቁ ጎልድማን ሳክስ ጋር ፈንዱን እንዲሰበስብለት 600 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ፈጽሞለት ነበር በወቅቱ።
ባንኩ በበኩሉ ቦንድ በመሸጥ በቢሊዮን ዶላሮች መሰብሰብ ችሎ ነበር። ገንዘቡ ግን እስከ አሁን የገባበት አልታወቀም።
ይህ ብዙ አገራትና ክፍለ አህጉራትን ያካለለው ማጭበርበር የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን ናጂብ ራዛቅን 12 ዓመት እስር እንዲፈርድባቸው ያደረገ ነው።
ቢሊየነሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛቅ አሁንም ይግባኝ እያሉ ነው።
ጎልድማን ሳክስ ይህ 'ተቋማዊ መደነቃቀፍ ነው እንጂ ሌላ አይደለም' ሲል ከቅሌቱ ራሱን ለማራቅ ሞክሮ አልፎታል።
ጎልድማን ሳክስ ባንክ ለዚህ 1ኤምዲቢ (1MDB) ተብሎ ለሚጠራው ሀሰተኛ ኢንቨስትመንት የ6 ቢሊዮን ዶላር ፈንድ ቦንድ በመሸጥ አሰባስቦ ነበር።
1ኤምዲቢ ፈንድ ማሌዢያን የኢሲያ ስቶክ ማርኬት ማእከል አደርጋለሁ ብሎ የተነሳና በርካታ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ለመግባት ቃል የገባ ሐሳዊ ቢዝነስ ነበር።
የኋላ ኋላ እንደተደረሰበት ተሰበሰብበ የተባለው ገንዘብ ብዙ ባንኮች እየተሽከረከረ፥ እየገባና እየወጣ በአመዛኙ እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ እስከዛሬም አለ።
ጉዳዩን ለዓመታት ሲመረምሩ የነበሩ የፋይናንስ መርማሪዎች ጎልድማን ሳክስ ቀጥተኛ አጭበርባሪ ባይሆንም ቦንድ እየሰበሰበ የነበረው ለተጭበረበረ ኢንቨስትመንት እንደሆነ የሚያሳዩ በርካታ ምልክቶች ነበሩ ብሏል።
ባንኩ ይህንን እያወቀ ነገሩን ቸል ብሎ ቆይቷል ብለው ይከሳሉ።
1ኤምዲቢ ፈንድ የማሊዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀኝ እጅ የሆነ ጆ ሎው የሚባል ሰው ከጀርባ ሆኖ ይዘውረው እንደነበር ተደርሶበታል።
በዚህ ቅሌት የተነሳ ሁለት የጎልድማን ሳክስ ባንክ ባልደረቦች የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በዚህ ወቅት የጎልደን ሳክስ ባንክ ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ሚስተር ሶሎሞን ደመወዛቸውና ጥቅማ ጥቅሙ አሁን ከተጠቀሰው 10 ሚሊዯን ዶላር ተጨማሪ የነበረ ሲሆን የቦርድ ዳይሬክተሮች ግን ከዚህ የ1ኤምዲቢ ቅሌት ጋር በተያያዘ ክፍያቸውን ቀንሶባቸዋል።
የሥራ አስፈጻሚው ደመወዝ 10 ሚሊዮኑ ዶላር ተቀንሶበትም ወደ 17 ሚሊዮን ተኩል ደርሷል።
ባንኩ ሚስትር ሶሎምን ስለዚህ የክፍለ ዘመኑ ማጭበርበር የሚያውቁት ነገር አልነበረም ሲል መስክሮላቸዋል።
ሚስተር ሶሎሞን ክፍያቸው 2 ሚሊዮን በካሽ፣ 4 ሚሊዮን በቦነስ መልክ፣ እንዲሁም 10 ሚሊዮን ከስቶክ ጋር በተያያዘ ማካካሻ ክፍያ ተደርጎ ነው የሚከፈላቸው። ደመወዛቸው እንደ የሥራ ዘመኑ ትርፍና ኪሳራ ከፍና ዝቅ የሚል ነው።
ጎልድማን ሳክስ ከዚህ የማጭበርበር ቅሌት ጋር በተያያዘ ለአራት አገራት 3 ቢሊዮን ዶላር መልሶ ለመክፈል ተስማምቶ ነበር።
ይህን ክፍያ ሲፈጽም ግን ከዚህ ማጭበርበር ጋር የተያያዙ ምርመራዎች ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙ በመጠየቅ ነው።
በ2012 እና በ2013 ብቻ ባንኩ ይህንን ቦንድ ሽያጭ ለማሌዥያው 1ኤምዲቢ ፈንድ ለመሰብሰብ ለሚሰራው ሥራ 600 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሎት ነበር።
ይህ የክፍለ ዘመኑ ማጭበርበር ተብሎ የሚጠራው የባንኩ ቅሌት በአሜሪካ፥ በዩኬ፥ በሲንጋፖር፣ በሆንግኮንግ ከፍተኛ ምርመራዎች ለዓመታት ሲደረጉበት ነበር።
ኮልድማን ሳክስ በዚህ የተጭበረበረ የቦንድ ሽያጭ ውስጥ በመሳተፉ ባንኩን 5 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ አሳጥቶታል።
ያም ሆኖ ባንኩ በተገባደደው የፈረንጆች ዓመት ትርፉ ወደ 44 ቢሊዮን ዶላር ተመንድጓል።
ጎልድማን ሳክስ እና 1ኤምዲቢ ፈንድ የገቡበት የቢሊዮን ዶላር ማጭበርበር ብዙዎች ሚዲያዎች የሆሊውዱ ሊዮናርዶ ዲካፕሪዮ የተወነበትን 'ዘ ዎልፍ ኦፍ ዎል ስትሪት' ፊልም ጋር ያመሳስሉታል።