ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ለአሜሪካ ሲሰልል ነበር ያለችውን ዜጋ በቁጥጥር ሥር አዋለች
ኢራን 'ለጠላት አገር አሜሪካ' ሲሰልል ነበር ያለችውን ዜጋዋን በቁጥጥር ሥር አዋለች።
ግለሰቡ በስም ባይጠቀስም ከዚህ ቀደም ተከሶ በዋስ የወጣና ክሱን ከውጭ ሆኖ እየተከታተለ የነበረ ሰው ነው ብላለች።
ሆኖም የክስ ሂደቱን ከውጭ ሆኖ እየተከታተለ ሳለ ተደብቆ ምዕራባዊ ድንበር አቋርጦ ሊያመልጥ ሲል ነው በቁጥጥር አዋልኩት ያለችው።
የኢራን መገናኛ ብዙሃን ባለፈው ሳምንት አንድ አሜሪካዊ ኢራናዊ ጥምር ዜግነት ያለው ነጋዴ ነኘ የሚል ኢማድ ሻርጊ የሚባል ሰው ድንበር በሕገ ወጥ መንገድ ሲያቋርጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ሲዘግቡ ነበር።
የዚህ ጥምር ዜግነት ያለው ግለሰብ መያዝና በስለላ ወንጀል መከሰስ ጆ ባይደን ከኢራን ጋር ሊጀምሩ ላሰቡት አዲስ ግንኙነት ደንቃራ እንዳይሆን ተሰግቷል።
ዶናልድ ትራምፕ ኢራን ላይ ጠንከራ ማዕቀብ በመጣል አገሪቱ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ምስቅልቅል ውስጥ እንድትገባ ምክንያት ሆነው እንደነበር አይዘነጋም።
የትራምፕ ፍላጎት የነበረው አሜሪካ በኦባማ ጊዜ የገባችበትን የ2015 የኑክሌር ስምምነት ቀዳዶ በመጣል ኢራንን ሌላ ጥብቅ የኑክሌር ስምምነት ውስጥ እንድትገባ ማስገደድ ነበር።
ይህን በማሰብም አሜሪካ በተናጥል ከስምምነቱ ወጥታ በአሜሪካ ላይ ከባድ የሚባሉ ማእቀቦችን በመጣል ቆይታ ነበር። ሆኖም ኢራን እጅ ሳትሰጥ ዶናለድ ትራምፕ ከዋይት ሐውስ ተሰናብተዋል።
ባይደን በበኩላቸው ኢራን ለስምምነቶች ታማኝ እስከሆነች ድረስ ወደ 2015ቱ የኑክሊየር ስምምነት መመለስ እፈልጋለሁ ማለታቸው አይዘነጋም።
ይህ ኢራንና አውሮጳዊያኑ የስምምነቱ ፈራሚዎች እየጠበቁት ያለው የባይደን ዳግም ወደ ስምምነት መመለስ በአሜሪካ ዜጋዎች በስለላ መከሰስ ሊያደናቅፈው ይችል ይሆን የሚል ስጋትን ፈጥሯል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢራን የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላቸውን በርካታ ዜጎች ለጠላት አገር አሜሪካ ትሰልላላችሁ በሚል ዘብጥያ ስታወርድ ነበር የሰነበተችው።
ማክሰኞ ዕለት የዐቃቢ ሕግ ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አገራቸው ኢራን ድርብ ዜግነትን በሕግ እንደማትቀበል ጠቅሰው ይህ በስም ያልተጠቀሰ አሜሪካዊ ዜግነት ያለው ግለሰብ ከዚህ ቀደም ለአሜሪካ መረጃ ሲቃርም ተደርሶበት ፍርድ ቤት በዋስ ሆኖ ክሱን እንዲከታተል የፈቀደለት ግለሰብ ነበር ብለዋል።
ሆኖም መረጃውን ይዞ በድንበር በኩል ሊያመልጥ ሲል ይዘነዋል ሲሉ አብራርተዋል።
ይህ በአንዲህ እያለ ባለፈው ሳምንት አሜሪካ አንድ ኢራናዊ የዩኒቨረስቲ ተመራማሪ በቦስተን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።
ካቬህ ሎትፎላህ አፍራይሳቢ የተባሉት እኚህ ሙሁር በቁጥጥር ሥር የዋሉት በምስጢራዊ መንገድ ለኢራን መንግሥት እየተከፈላቸው የመረጃ ማቀበል ሥራ ይሰራሉ በሚል ነው።