ፑቲን ቅንጡው ቤተ መንግሥት ‘የኔ አይደለም’ አሉ

የሩስያዊ ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ በቀንደኛ ተቀናቃኛቸው አሌክሲ ናቫንሊ ቪድዮ ላይ የታየው ቅንጡ ቤተ መንግሥት የእሳቸው አለመሆኑን አስታወቁ።

የፑቲን ቤተ መንግሥት የተባለውን የምርመራ ቪድዮ ከ86 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመልክተውታል። ፑቲን ግን ቤተ መንግሥቱ "የኔ አይደለም" ብለዋል።

ብላክ ሲ አቅራቢያ የተገነባው ቤተ መንግሥት የፑቲን የቅርብ ወዳጅ በሆኑ ቢልየነሮች ገንዘብ እንደተሠራ በቪድዮው ተገልጿል።

መቆመሪያ፣ ወይን ማቀነባበሪያና ሌሎችም አገልግሎቶች ያሉት ይህ ቤተ መንግሥት በሕገ ወጥ ገንዘብ እንደተሠራ ተቃዋሚው ናቫንሊ ተናግሯል።

ከጀርመን ወደ ሩስያ ካቀና በኋላ የታሰረው ናቫንሊ እንዲፈታ በመጠየቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሩስያውያን ሰልፍ አካሂደዋል።

የ44 ዓመቱ ታቃዋቂ ተቃዋሚ ተመርዞ ለሞት ተቃርቦ ነበር። ለመመረዙ ተጠያቂው ፑቲን ነው ቢልም ክሬምሊን ክሱን አጣጥሏል።

ፑቲን ቪድዮውን የገለጹት "የምስል ስብስብ" እና "አሰልቺ" በማለት ነው።

"እዛ በኔ ስም የተቀመጠ ንብረት የኔ ወይም የቅርብ ዘመዶቼም አይደለም" ሲሉ ፑቲን ተናግረዋል።

ሙሉ ቪድዮውን ለማየት ጊዜ እንዳልነበራቸውና ቅንጭብጫቢ መመልከታቸውን ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል።

አያይዘውም ናቫንሊን በሚደግፍ ሰልፍ ላይ ታዳጊዎች መሳተፍ እንደሌለባቸውና ፓሊሶች ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል።

"ማንም ሰው የፓለቲካ ፍላጎቱን እና ግቡን በተቃውሞ ለማሳካት መሞከር የለበትም" ሲሉ ፑቲን ተቀናቃኛቸው ናቫንሊን ወርፈዋል።

ናቫንሊ ከታሰረ በኋላ አብሮት የሚሠራው ቡድን የምርመራ ቪድዮውን ለቋል። ቪድዮው ላይ እንደተባለው ከሆነ ቅንጡው ቤተ መንግሥት 1.37 ቢሊዮን ዶላር ፈሶበታል።

ይህንንም "በታሪክ ከባዱ ሙስና" ሲል ናቫልኒ በቪድዮው ኮንኗል።

ናቫንሊ በቪድዮው "በዚህ ገንዘብ ለአለቃቸው ቤተ መንግሥት ሠርተዋል" ብሏል።

የሩስያ ብሔራዊ የምርመራ ተቋም ቤተ መንግሥቱ ዙርያ ያለው 27 ስኩዌር ማይል መሬት ባለቤት እንደሆነም በቪድዮው ተጠቁሟል።

ባለፈው ሳምንት ክሬምሊን ቤተ መንግሥቱ የፑቲን አይደለም ብሎ ማስተባበሉ አይዘነጋም።