ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቦኮ ሃራም የናይጄሪያ ተማሪዎችን አግቻለሁ አለ
ከሰሞኑ ለጠፉትና ለታገቱት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድ ተማሪዎች ኃላፊነቱን ፅንፈኛው ቦኮ ሃራም ወስዷል።
በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ በሚገኝ የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ጥቃት ከደረሰ በኋላ በመቶዎች የሚቆጠሩት ተማሪዎች እንደጠፉና ሳይታገቱም እንዳልቀሩ ሪፖርት ተደርጓል።
ተማሪዎቹ የታገቱት በቦኮ ሃራም ከሆነ ፅንፈኛው ቡድን በቀጠናው እያደረገው ያለው መስፋፋት አስጊ ነው ተብሏል።
አራት ደቂቃ ባለው የድምፅ መልዕክት የቦኮ ሃራም መሪ ነኝ ያለው አቡባከር ሼካው ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው የምዕራባውያንን ትምህርት ነው።
አስር አመት እድሜ ያላቸው ህፃናትም ከጠፉትም መካከል ይገኙበታል።
ተማሪዎቹ የጠፉበት ግዛት ካትሲና አስተዳዳሪ 333 ተማሪዎች መጥፋታቸውን አስታውቆ፤ ከታገቱበትም ለማስለቀቅ ድርድሮች እየተካሄዱ ነው ብለዋል።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ የትውልድ ቦታ በሆነችው ካትሲና የደረሰው ጥቃትም መንግሥት በደህንነት ቁጥጥር ላይ ያለውን ቸልተኝነት ያሳየ ነው በሚልም ከፍተኛ ትችት እየደረሰበት ነው።
በሃምሌ ወር ቡድኑ ባወጣው ቪዲዮ ግዛቱን እያስፋፋ መሆኑንና በአገሪቷ ሰሜን ምዕራብ ክፍልም መግባቱን አስታውቋል።
በአካባቢው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መንግሥት "ሽፍቶች" አደረሱት ባሉት ጥቃቶች ተገድለዋል።
እነዚህ "ሽፍቶች የተባሉት የወንጀለኞች ቡድን ከቦኮ ሃራም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ይኑረው ግልፅ አይደለም።
ሆኖም ከአልቃይዳ ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው የሚባለው አንሳሩ የተባለ ሌላ ቡድን በግዛቲቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሳል።
ቦኮ ሃራም ከ2009 ጀምሮ አስከፊ የሆነ የሽምቅ ውጊያ እያካሄደ ሲሆን በተለይም በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ በኩልም አትኩሮቱን አድርጓል ።
በዚህም ግጭት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል እንዲሁም ከሁለት ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችም ቤት ንብረታቸውን ትተው ተፈናቅለዋል።