የሕዝብ ቁጥር ማሽቆልቆል ያሳሰባት ጃፓን ውሃ አጣጭ ለሚያገናኙ ገንዘብ ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሕዝብ ቁጥር መቀነስ ያሳሰባት ጃፓን ጥንዶችን ለሚያገናኝ መተግበሪያ የገንዘብ ድጎማ እንደምታደርግ አስታውቃለች።
ሰው ሠራሽ ልህቀት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) ተጠቅመው ጃፓናውያን የፍቅር ጓደኛ እንዲያገኙ የሚያግዙ ግዛቶች ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ የገንዘብ ማበረታቻ ከጃፓን መንግሥት ይሰጣቸዋል።
አምና በጃፓን የተወለዱ ልጆች ቁጥር ከ865,000 በታች ሆኗል። ቁጥሩ እስካሁን ከታየው እጅግ ዝቅተኛው ነው።
ጃፓን የአዛውንቶች አገር ሆናለች። በዓለም ዝቅተኛ የወሊድ መጠን ካላቸው አንዷም ናት።
ለመተግበሪያዎች የገንዘብ ፈሰስ ማድረግ የልጆችን ቁጥር ለመጨመር ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል ይጠቀሳል።
በሚመጣው ዓመት ለሚተገበረው ፕሮጀክት 19 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ጥንዶች አገናኞች
ሰዎች ውሃ አጣጭ እንዲያገኙ የሚያግዙ ተቋሞች ሰው ሠራሽ ክህሎት መጠቀም ጀምረዋል።
ከዚህ ቀደም በሰው ኃይል ታግዘው ይሠሩ የነበሩት ተቋሞች፤ ቴክኖሎጂው የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ያምናሉ። የፍቅር አጋር ለማግኘት የሚቀርቡ ማመልከቻዎችን በተሻለ መንገድ መገምገምም ይችላሉ።
እነዚህ ተቋሞች ሰዎችን ሲያገናኙ ከግምት የሚያስገቡት እድሜ፣ ወርሀዊ ገቢና የመሳሰሉትን ነው። እነዚህ መስፈርቶች ደግሞ ትክክለኛውን አቻ አያገናኙም።
መንግሥት ለመተግበሪያዎች ድጋፍ ማድረግ ሲጀምር አሠራሩ ይዘምናል ተብሎ ይጠበቃል። ሰዎች የትርፍ ጊዜያቸውን በምን ያሳልፋሉ? የሕይወት መርሀቸው ምንድን ነው? በሚሉት መስፈርቶች መሠረት እንዲገናኙ ይደረጋል።
አንድ የምክር ቤት አባል ለኤኤፍፒ "ኤአይን ተጠቅመው ጥንዶችን ለሚያገናኙ ግዛቶች ድጋፍ ለማድረግ አቅደናል። የልጆች ቁጥርን ለመጨመር ይረዳል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
እአአ 2017 128 ነበረው የጃፓን የሕዝብ ቁጥር በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ ደግሞ ቁጥሩ ወደ 53 ሚሊዮን እንደሚወርድ ተፈርቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"የፍቅር ግንኙነት መመስረት ካልፈለጉ ውሃ አጣጭ መተግበሪያው ውጤት አይኖረውም"
የማኅበራዊ፣ ባህላዊ እና ሕክምና ጥናት ባለሙያዋ ዶ/ር ሳችኮ ሆሪጉቺ፤ መንግሥት ጥንዶችን የሚያገናኙ መተግበሪያዎችን ከመደገፍ የተሻለ አማራጭ አለው ትላለች።
እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው ወጣቶች የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ማስቻልን ነው።
ባለሙያዋ በማስረጃነት የምታቀርበው አንድ በቅርቡ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወጣቶች የፍቅር ግንኙነት የመመስረት ፍላጎት አያሳዩም።
"የፍቅር ግንኙነት መመስረት ካልፈለጉ ውሃ አጣጭ መተግበሪያው ውጤት አይኖረውም" ብለዋል።
ባለ ሥራ ጃፓናዊ እናቶች ድጋፍ እንደማያገኙ ብዙ ተንታኞች ይናገራሉ። ሴቶች ልጅ እንዲንከባከቡ፣ የቤት ሥራን እንዲያከናውኑና ከነዚህ በተጨማሪ የቢሮ ሥራም እንዲሠሩ ይጠበቃል።
መንግሥት ሴቶች የሙሉ ጊዜ ሥራ እንዲኖራቸው አበረታታለሁ ቢልም የፆታ ክፍተቱ ሰፊ ነው።
አምና የወጣ የፆታ እኩልነት ሰንጠረዥ ላይ ጃፓን ከ153 አገሮች መካከል 121ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ከዛ ቀደም ከነበራት 11 ደረጃ ዝቅ ማለቷን የወርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም አሃዝ ያመለክታል።












