ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይ ምርቶቿ ላይ ማዕቀብ እንዳይጣል የመካከለኛው ምሥራቅ አገራትን ጠየቀች
ፈረንሳይ የተለያዩ ቁሳቁሶቿ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚደረጉ ቅስቀሳዎችን የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እንዲያስቆሙ ጠየቀች።
ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ ነብዩ መሐመድን የሚያሳዩ ካርቱኖችን መሣል ይቻላል የሚል አቋም ማንጸባረቃቸውን ተከትሎ የፈረንሳይ እቃዎች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጥሪ እየተደረገ ነው።
በኩዌት፣ ጆርዳን እና ካታር የሚገኙ አንዳንድ መደብሮች የፈረንሳይ ምርቶችን ማስወገድ ጀምረዋል። በሊቢያ፣ ሶርያ እና የጋዛ ሰርጥ ተቃውሞ ተካሂዷል።
ፈረንሳያዊ መምህር ሳሙኤል ፓቲ፤ የነብዩ መሐመድን የካርቱን ሥዕል ለተማሪዎቹ ካሳየ በኋላ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉ ይታወሳል። ክስተቱን ተከትሎ ፕሬዘዳንት ማክሮን "ኢስላሚስቶች ነጋችንን መቆጣጠር ይፈልጋሉ። ፈረንሳይ ግን ካርቱን መሥራት አታቆምም" ብለው ነበር።
የነብዩ መሐመድን እንዲሁም የአላህን ምስል ማሳየት በእስልምና የተከለከለ ነው። የማክሮን ንግግርም ቁጣ ቀስቅስሷል።
ፈረንሳይ ከሃይማኖት ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነች አገር እንደሆነች ትገልጻለች። የአንድ ማኅበረሰብን ስሜት ላለመጉዳት በመጠንቀቅ ውስጥ የንግግር ነጻነት መገደብ የለበትም የሚል አቋም ታንጸባርቃለች።
ማክሮን "መቼም ቢሆን እጅ አንሰጥም" ሲሉ ትዊት አድርገዋል።
በቱርክ እና በፓኪስታን ያሉ የፖለቲካ መሪዎች ማክሮንን ተችተዋል። የሃይማኖት ነጻነትን እየተጋፉ እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፈረንሳይ የሚኖሩ ሙስሊሞችን እያገለሉ እንደሆነም ገልጸዋል።
የቱርኩ ፕሬዘዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ማክሮን ስለ እስልምና ያላቸውን አቋም በተመለከተ "አእምሯቸውን ይመርመሩ" ብለዋል።
ፈረንሳይ ቱርክ ከሚገኙ አምባሳደሯ ጋር ለመምከር ወደ ፈረንሳይ ጠርታቸዋለች።
የፓኪስታኑ መሪ ኢምራን ከሀን "እስልምናን ሳይገነዘቡ ሃይማኖቱን እያጥላሉ ነው" ብለዋል።
በወሩ በባቻ ላይ ማክሮን "እስላማዊ ገንጣይ" ያሏቸው ቡድኖች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረው ነበር።
የምዕራብ አውሮፓ ትልቁ የሙስሊም ማኅበረሰብ ማክሮን፤ ሃይማኖታዊ ጫና እያደረጉባቸው እንደሆነና እንቅስቃሴያቸው ሙስሊም ጠል እንደሆነ ተናግረዋል።
እአአ 2015 ላይ የፈረንሳዩ ሽሙጥ አዘል መጽሔት ቻርሊ ሄድቦ ላይ በተሰነዘረ ጥቃት 12 ሰዎች መገደላቸው አይዘነጋም። መጽሔቱ የነብዩ መሐመድን ካርቱን አትሞ ነበር።
የፈረንሳይ ምርቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የተደረገው ቅስቀሳ
ባሳለፍነው እሑድ በጆርዳን፣ ካታር እና ኩዌት ያሉ አንዳንድ መደብሮች የፈረንሳይ ምርቶችን አስወግደዋል። የፈረንሳይ ውበት መጠበቂያ ምርቶች ከመደርደሪያ ተነስተዋል።
ክዌት ውስጥ ትልቁ የአከፋፋዮች ማኅበር የፈረንሳይ ምርቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል አዟል።
የሸማቾች ማኅበርም በተደጋጋሚ ነብዩ መሐመድን የሚያጥላሉ አስተያየቶች በመሰንዘራቸው ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
የፈረንሳይ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ባወጣው መግለጫ "ምርቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የተደረገው ጥሪ መሠረተ ቢስ ነው። ይህ ጥሪና በጥቂት አክራሪዎች የሚጫሩ አገሪቱ ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች መገታት አለባቸው" ብሏል።
በሳኡዲ አረቢያ እንዲሁም በሌሎች የአረብ አገራትም የፈረንሳይ ምርቶች ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሚጠይቁ የበይነ መረብ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።
የፈረንሳዩ መደብር ካርፉር እንዲዘጋ የሚጠይቀው ሀሽታግ፤ በሳኡዲ የትዊተር ተጠቃሚዎች ዘንድ ከነበሩ አነጋጋሪ ጉዳዮች ሁለተኛውን ደረጃ ይዟል።
በሊቢያ፣ ጋዛ እና ሶርያ ፈረንሳይን የሚያወግዙ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል።