ፈረንሳይ፡ ቻርሊ ሄብዶ መፅሄት አወዛጋቢውን የነብዩ መሐመድ ካርቱንን እንደገና አተመ

ቻርሊ ሄብዶ የተሰኘው የፈረንሳዩ ቧልት ቀመስ መፅሄት ከአምስት ዓመታት በፊት ለሽብር ጥቃት ያጋለጣቸውን የነብዩ መሐመድን ምስል በካርቱን እንደገና አውጥቷል።

የሽብር ጥቃቱን በዋነኝነት ያቀነባበሩት ሁለት ፅንፈኛ አክራሪዎችና እነሱንም በመርዳት አስራ አራት ግለሰቦች የፍርድ ሂደት በነገው እለት የሚጀመር ይሆናል።

የመፅሄቷ ጋዜጠኞች ስብሰባ ላይ እያሉ በተሰነዘረው ጥቃት ታዋቂ ካርቱኒስቶችን ጨምሮ አስራ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል። በዚያኑ ቀንም እንዲሁ በፓሪስ በደረሰ ሌላ ጥቃት አምስት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

ይህንንም ተከትሎ ፀረ- ጂሃድ ተቃውሞዎች ፈረንሳይን አጥለቅልቀዋት ነበር።

መፅሄቱ በፊት ገፁ ላይ በአሁኑ ወቅት ይዞት የወጣው የነብዩ መሃመድን የሚወክል አስራ ሁለት ካርቱኖችን ናቸው። እነዚህ ካርቱኖች በቻርሊ ሄብዶ መፅሄት ላይ ከመውጣታቸው በፊት አንድ የዴንማርክ ጋዜጣ ነበር መጀመሪያ ይዞት የወጣው።

በአንደኛው ካርቱንም ላይ ነብዩ መሃመድ በተርባን ጥምጥም ፈንታ ቦምብ ጭንቅላታቸው ላይ ይታያል። በፈረንሳይኛም "ይሄ ሁሉ የደረሰው ለዚህ ነበር" የሚልም መልዕከትን አስፍሯል።

መፅሄቱ በርዕሰ አንቀፁም ላይ እንዳሰፈረው ከአምስት አመት በፊት የደረሰውን ጥቃት ተከትሎም የነብዩ መሐመድን ተመሳሳይ ካርቱን እንዲያትሙ ከፍተኛ ጥያቄ እንደቀረበላቸው ነው።

"ተመሳሳይ ካርቱኖች እንድናትም ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖርም ፈቃደኛ አልነበርም። ህጉ ቢፈቅድልንም ምክንያት አልነበረንም። በአሁኑ ሰዓት ግን ጥቃቱን ያደረሱት ግለሰቦች የፍርድ ሂደት በሚጀመርበት ሳምንት መሆኑ እንደገና ማተሙ ትርጉም አለው" በማለት አስፍሯል።

በፍርድ ሂደቱ ምን ይጠበቃል?

የቻርሊ ሄብዶ የፓሪስ ቅርንጫፎቹን ጨምሮ፣ በአይሁዶች ባለቤትነት የሚገኝ መደብር ጥቃት ደርሶባቸዋል። አንድ ፖሊስ እንዲሁ የሽብር ጥቃቱ ኢላማ ሆኗል።

ሶስቱ ተጠርጣሪዎች በሌሉበት ጉዳያቸው የሚታይ ሲሆን ወደ ሶሪያና ኢራቅ ሳይሄዱም አልቀሩም ተብሏል።

በፍርድ ሂደቱ ላይ ከጥቃቱ የተረፉትን ጨምሮ፣ ወዳጅ ዘመድ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ 200 የሚጠጉ ምስክሮች እንደሚሰሙበትም የፈረንሳዩ አርኤፍአይ ዘግቧል።

ፍርዱ መጋቢት ላይ ይጀመራል ተብሎ ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሟል። ሂደቱም እስከ ህዳር ድረስ ይቆያል ተብሏል።

ቧልት ቀመስ የሆነው ቻርሊ ሄብዶ በቀኝ አክራሪዎች ላይ በመዘባበት በርካታ ስራዎችን የሚያቀርብ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በካቶሊክ፣ ይሁዲና እስልምና እምነቶችም ላይ ፌዝና ቀልድ ማቅረቡ አወዛጋቢ አድርጎታል።

ሆኖም ነብዩ መሃመድን በካርቱን ማሳየታቸው በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት ኢላማ አድርጓቸዋል።

መፅሄቱም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ነው በሚል ካርቱኑን ደግፎ አዘጋጁ ስቴፈን ቻርቦኒየር (ቻርብ) ተከራክሯል " ሙስሊሞች በስዕላችን ስላልሳቁ ምንም አልላቸውም። እኔ የምኖረው በቁርዓን ህግ ስር ሳይሆን በፈረንሳይ ህግ ነው" በማለት በ2012 መናገሩንም አሶሺየትድ ፕሬስ አስነብቦ ነበር።

በ2015 ጥቃት በኋላም በርካቶች " እኔ ቻርሊ ነኝ" በሚልም ለመፅሄቱ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል።

በአወዛጋቢነቱና በቆስቋሽነቱ በአለም የገነነው መፅሄቱም የሌሎችን እምነት እንዲያከብርም ከፍተኛ ትችት እንደደረሰበትም የጋዜጣው ስራ አስኪያጅ ጄራርድ ቢያር ለቢቢሲ ጥቃቱ ከደረሰ ከአመት በኋላ ተናግረው ነበር።