ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይጄሪያ በተቀሰቀሰው የተቃውሞ ሰልፍ ምክንያት ለተማሪዎች የሚሰጠውን ፈተና ሰረዘች
ናይጄሪያ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለመስጠት አስባ የነበረው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንዲቋረጥ አዘዘች።
የናይጄሪያ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በተቃዋሚ ሰልፈኞችና በፖሊስ መካከል ግጭቶች እየተባባሱ በመምጣታቸው ነው።
ናይጄሪያውያን የፖሊስ ጭካኔን በመቃወም አደባባይ መውጣት ከጀመሩ ሳምንት አልፏቸዋል።
በንግድ ከተማዋ ሌጎስ፣ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች የፖሊስ ጭካኔን በመቃውም አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች በርከት ብለው ታይተዋል።
ማክሰኞ እለት በሌጎስ ፖሊስ ሰልፈኞቹ ላይ ከተኮሰ እና ሰዎች ከሞቱ በኋላ፣ የተቆጡ ተቃዋሚዎች ሕንጻዎችን አቃጥለዋል፣ ዘርፈዋል፣ እንዲሁም ማረሚያ ቤቶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል።
የብሔራዊ ፈተና ምክር ቤት አክሎ እንዳስታወቀው ፈተናው እንዳይሰጥ ውሳኔውን ያስተላለፈው የተጣለውን ሰዓት እላፊም ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው።
ምክር ቤቱ አክሎም ፈታኞች ወደ ጣብያዎቻቸው በመመለስ ተጨማሪ ውሳኔ እስኪተላለፍ ድረስ እንዲጠባበቁ እንደተነገራቸው ገልጿል።
የሁለተኛ ደረጃ ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች የሚለዩበት ነው።
የፈተናዎች ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ሕዳር ወር አጋማሽ ላይ ፈተናው ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
ሐሙስ እለት ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ተቃውሟቸውን በማቆም ከመንግሥት ጎን በመሆን "መፍትሄ በመፈለግ" እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።
አምንስቲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ማክሰኞ እለት በሌጎስ ከተማ ቢያንስ 12 ሰዎች ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መሞታቸውን ተናግሯል።
ማክሰኞ እለት በሌጎስ ሌኪ በምትባል ስፍራ ፖሊስ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ተኩሶ ከአስር በላይ ሰዎችን ከገደለ በኋላ የንግድ ተቋማት፣ ፖሊስ ጣብያዎች፣ የመንግሥት ድርጅት ሕንጻዎች ተዘርፈዋል፤ ተቃጥለዋል።
የንግድ ከተማዋ ሌጎስ የወትሮው እንቅስቃሴዋ ተቋርጦ ፀጥ ረጭ ብላ ከርማለች።
የተቃጠሉ ጎማዎች በየጎዳናው ላይ የሚታዩ ሲሆን፣ በዋና መንገድ የሚንቀሳቀሱ እግረኞችም የታጠቁ አለመሆናቸወን ለማሳየት እጃቸውን ከፍ አድርገው ሲሄዱ ተስተውለዋል።
በከተማዋ የ24 ሰዓት እላፊ የተጣለ ሲሆን ወጣቶችም ውስጥ ለውስጥ መንገድ ዘግተው እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማድረጋቸው ተስተውሏል።