ናይጄሪያ ልዩ የፖሊስ ኃይል ይወገድ በሚለው ተቃውሞ ትምህርት ቤቶቿን ዘጋች

በፖሊስ የበትር ጭካኔ የተማረሩ ናይጄሪያውያን ሳርስ ተብሎ የሚጠራው የፌደራል ፖሊስ ልዩ ኃይል ይበተን የሚለውን ተቃውሞ ተከትሎ በናይጄሪያዋ የንግድ መዲና ሌጎስ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተወስኗል።

የትምህርት ሚኒስቴሩ ኮሚሽነር ፎልሳዴ አደፊሳዮ እንደተናገሩት የተማሪዎቹ፣ የመምህራኑ እንዲሁም አጠቃላይ የሰራተኞቹን ደህንነት ዋስትና መስጠት ስላልተቻለ ለመዘጋታቸው ምክንያት ሆኗል።

ትምህርት ቤቶቹ ተመልሰው መቼ እንደሚከፈቱ በቅርቡ ይነገራል ተብሏል።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቶቹ የርቀት ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች አማራጮችን ሊጠቀሙ ይገባል ተብሏል።

የፖሊስ ጭካኔን የሚቃወሙ ሰልፈኞች የከተማዋን አለም አቀፍ አየር ማረፊያ የሚወስደውን መንገድ መዝጋታቸውን ተከትሎም ተቃውሞ ተጧጡፏል።

በዚህ ሳምንት ሰኞም በተለያዩ የአገሪቷ ከተሞችም ተቃውሞው ተዛምቷል።

ከዚህም በተጨማሪ በመዲናዋ አቡጃ፣ ቤኒንና ካኖ የነበሩት የተቃውሞ ሰልፎች ከፍተኛ ረብሻ እንደነበረባቸውም ተገልጿል።

ፖሊሶች አንድን ሰው ሲገድል የሚያሳይ ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎም ነው ተቃውሞቹ የተቀጣጠሉት።

እነዚህ ተቃውሞዎች በተለይም ዘረፋን ለማስቆም የተቋቋመውን ልዩ የፌደራል ፖሊስ ኃይል ወይም ሳርስ ተብሎ የሚታወቀው ላይ ያነጣጠሩ ሲሆኑ፤ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ሰዎችን ማሰር፣ ማሰቃየትና ግድያም ይፈፅማል በሚልም ከፍተኛ ውግዘትም ቀርቦበታል።

ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበበት ሳርስ እንዲበተን ቢደረግም የሳርስ አባላት በሌሎች የፖሊስ ክፍሎች እየተሰማሩና እየተመደቡ ነው የሚሉ ጉዳዮች መሰማታቸውን ተከትሎም እንደገና ተቃውሞቹ የቀጠሉት።

ሰልፈኞቹ እነዚህ የሳርስ አባላት ለፈፀሙት ወንጀል ህግ ፊት መቅረብ አለባቸውም እያሉ ነው።

ከሰሞኑ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት "ስር ነቀል" የፖሊስ ማሻሻያ እንደሚደረግና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል የተባሉትም የሳርስ አባላት ወደ ፍርድ ይቀርባሉ ብለው ነበር።