አሜሪካ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት 2.9 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ድጋፍ አደረገች

አሜሪካ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት 2.9 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ድጋፍ አደረገች

አሜሪካ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን አቅም ለማጠናከር የሚውል የሥልጠና እና የቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጓን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ አስታወቀ።

በዚህ ወር አሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት 2.9 ሚሊየን ዋጋ የሚያወጣ የሥልጠናና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል።

ድጋፉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አል-ሻባብ እና ሌሎች አሸባሪ ቡድኖች የሚያደርሱትን አደጋ ለመመከት የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲው ገልጿል።

ድጋፍ ከተደረጉ ቁሳቁሶች መካከልም ላንድ ክሩዘር ተሽከርካሪዎች፣ የወታደር ተሽከርካሪዎች፣ አምቡላንስ፣ የጭነትና የነዳጅ መኪናዎች፣ የውሃ ማጠራቀሚያዎች፣ ለዘመቻ ማዕከላት የሚሆኑ ኮምፒዩተሮች እና ለምሽት አሰሳ የሚውሉ መሳሪያዎች ይገኙበታል።

የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የገለፀው ኤምባሲው፤ የተደረገው ድጋፍም የዚሁ አካል መሆኑን አስታውሷል።

አሜሪካ እና ኢትዮጵያ የወታደራዊ ስልጠና፣ የሰላም ማስከበር እንዲሁም የፀረ ሽብር ዓላማዎችን የሚደግፉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያካተተ ለረዥም ጊዜ የቆየ አጋርነት ፈጥረዋል።