በአርሜኒያና በአዘርባጃን መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ቢያንስ 100 ሰዎች ሞቱ

በቀድሞው የሶቪየት ሪፐብሊክ አካል በነበሩት አርሜኒያና አዘርባጃን መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰላማዊ ሰዎችን ጨምሮ ቢያንስ 100 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

በሁለቱ አገራት መካከል ግጭቱ የተቀሰቀሰው በናጎርኖ- ካራባክህ ግዛት ይገባኛል ጥያቄ ጋር ተያይዞ ነው።

ተራራማው በናጎርኖ ካራባክህ ግዛት የአዘርባጃን አካል እንደሆነ ቢታወቅም፤ ከጎርጎሮሳዊያኑ 1994 ጦርነት ማብቂያ ወዲህ ግን የሚተዳደረው በአርሜኒያዊያን ነው።

ራስ ገዝ አስተዳደሯ ከእሁድ እለት ጀምሮ 84 ወታደሮች እንደሞቱባት ያስታወቀች ሲሆን ንፁሃን ዜጎችም ከተጎጂዎቹ መካከል ይገኙበታል ተብሏል።

አዘርባጃን ግን ምን ያህል ወታደሮች እንደሞቱባት ባትገልፅም፤ ሰባት ንፁሃን ሰዎች መሞታቸውን ግን ገልፃለች።

ማክሰኞ ዕለት የአርሜኒያ መከላከያ ሚኒስተር በአርሜኒያ ምስራቃዊት ከተማ ቫርዴኒስ አንድ የመንገደኞች አውቶብስ በአዘርባጃን ሰው አልባ አውሮፕላን መመታቱን ተናግረዋል። ነገር ግን በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተባለ ነገር የለም።

ከአንድ ቀን በፊት ከአንድ ቤተሰብ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎም፤ አዘርባጃን ሁለት ሰላማዊ ሰዎች በአርሜኒያ መገደላቸውን አስታውቃለች።

ግጭቱ ከአራት ዓመታት ወዲህ የታየ ከባድ ግጭት ነው ተብሏል።

ይህንን ተከትሎም ማክሰኞ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ውይይት ሊያካሂድ መሆኑ ተገልጿል።

አርሜኒያ እና አዘርባጃን በርካታ ወታደሮችን በማንቀሳቀስ በተወሰኑ አካባቢዎች ወታደራዊ ሕግ በማወጅ ግጭቱ ለመጀመሩ አንዳቸው በአንዳቸው ሲያሳብቡ ነበር።

በግጭቱ ሌሎች አገራት በቀጥታ ሊሳተፉ ይችላሉ የሚል ስጋቶችም ተፈጥረዋል።

ቱርክ አዘርባጃንን በግልፅ መደገፍ የጀመረች ሲሆን በአርሜኒያ ወታደራዊ ካምፕ ያላት ሩሲያ ደግሞ ሁለቱ አገራት በአስቸኳይ ተኩስ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርባለች።

ስለ ናጎርኖ- ካራባክህ

  • ተራራማ አካባቢ ሲሆን 4 ሺህ 400 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት አለው
  • ክርስቲያን አርሜኒያዊያንና ሙስሊም ቱርካዊያን ይኖሩበታል።
  • በቀድሞ የሶቭየት ሕብረት ጊዜ በአዘርባጃን ሪፐብሊክ ሥር ራሷን የቻለች ክልል ነበረች።
  • የአዘርባጃን ግዛት እንደሆነችም ዓለም አቀፍ እውቅና አላት፤ ነገር ግን አብዛኞቹ ሕዝቦቿ አርሜኒያዊያን ናቸው።
  • ከጎርጎሮሳዊያኑ 1988-1994 ድረስ በተካሄደው ጦርነት አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን 30 ሺህ የሚጠጉ ደግሞ ተገድለዋል።
  • ተገንጣይ ኃይሎች ተጨማሪ የአዘርባጃንን ግዛት ይዘዋል።
  • ቱርክ አዘርባጃንን በግልፅ ትደግፋለች
  • ሩሲያ ደግሞ በአርሜኒያ ወታደራዊ ካምፕ አላት