ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ዘረኛ ሃውልቶች መገርሰሳቸውን ደገፉ
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጨቋኝ የሚባለውን የነጮች አፓርታይድ አገዛዝን የሚያንፀባርቁ ሃውልቶች እንዲገረሰሱ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት "ዘረኝነትን ከፍ የሚያደርግ የትኛውም ምልክትም ሆነ ሃውልት እንዲሁም ያንን አስጠሊታ የታሪክ ዘመናችንን የሚያስታውስ ማንኛውም ድርጊት በዲሞክራሲያዊቷ ደቡብ አፍሪካ ቦታ የለውም" በማለት ተናግረዋል።
"ያንን የተከፋፈለ የታሪክ ጊዜን ከፍ አድርገው የሚያሳዩ ሃውልቶች ሊነሱ ይገባል" በማለትም በትናንትናው ዕለት አገሪቷ ሄሪቴጅ የተባለውን በዓሏን በምታከብርበት እለት ተናግረዋል። ሄሪቴጅ የተባለው ክብረ በዓል በአገሪቷ ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ባህሎችን ቦታ በመስጠትም የሚከበሩበት እለት ነው።
የነዚህ ሃውልቶች መገርሰስ ታሪክን የማጥፋት ወይም የመደምሰስ አካል ተደርጎ መታየት እንዳለበት ያስታወሱት መሪው ነገር ግን "በአገሪቱ ውስጥ የተጨቆኑ ህዝቦች ያለፉበትን ሁኔታ ቦታ መስጠትና ለነሱ ማሰብ ያስፈልጋል" ብለዋል።
አክለውም "ሃውልቶቹን ለመገርሰስ ማሰባችን ይቅርታ የምንጠይቅበት አይደለም ምክንያቱን የምንተባበርባት አገርን መፍጠር ስለምንፈልግ ነው" ብለው አፅንኦት ሰጥተዋል።
ዘረኛውንና ጨቋኙን የአፓርታይድን አገዛዝ የሚወክሉ ሃውልቶችን ለመገርሰስ በባለፉት አመታት ከፍተኛ ዘመቻ እየተካሄደ ነው።
ከዚህ ቀደም በደቡብ አፍሪካዋ ኬፕታውን የእንግሊዛዊውን ቅኝ ገዥ ሰሲል ሮድስ ሃውልት ጭንቅላት መቆረጡ ይታወሳል።።
በነጭ ፖሊስ ተደፍቆ የተገደለውን ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድን ሞት ተከትሎ የበርካታ ባርያ ፈንጋዮች፣ ጨፍጫፊዎችና ዘረኞች ሃውልት ተገርስሷል።
ከዚህም በተጨማሪ በመላው አለምም ከፍተኛ ተቃውሞንም አቀጣጥሏል።
ነጭ ፅንፈኛውና ዘረኛው ሮድስ የእንግሊዝን ቅኝ ግዛት በ19ኛው ክፍለ ዘመን የመራ ሲሆን፤ ደቡብ አፍሪካንም እንደ ሰም አቅልጦ በመግዛት ማዕድኗን በዝብዟል፤ ሃብትንም አፍርቷል።
በርካቶችም የኢምፔሪያሊዝምና የዘረኝነትም ሃውልት ስለሆነ ሃውልቱ ይገርሰስ በሚልም ዘመቻ ተደርጓል።
የሮድስ ማስታወሻ ሃውልት በኬፕታውን የቆመው በጎርጎሳውያኑ 1912 ነበር።
ሃውልቱ መጀመሪያ ላይ ጉዳት የደረሰበት በጎርጎሳውያኑ 2001 ሲሆን ቀይ ቀለምም ተደፍቶበት ነበር።
ከሶስት አመት በፊትም አፍንጫው ተቆርጦ እንደገና ታድሷል።
በኬፕታውን ዩኒቨርስቲ የሚገኘው የቀድሞው ቅኝ ገዥ ሃውልት በጎርጎሮሳውያኑ 2015 "ጨፍጫፊዎችና ቅኝ ገዥዎች መውደቅ" አለባቸው የሚለውን ከፍተኛ ተቃውሞ እንዲገረሰስ ተደርጓል።
በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ታሪክ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ጨካኙ ሮድስ በስሙም የአሁኗን ዚምባብዌ የቀድሞዋን ሮዴዥያ በሚልም ገዝቷል።
እንግሊዛውያን ከሁሉም ዘሮች የተመረጡ ናቸው የሚልም ጭፍንና ጠባብ ነበርም ይባላል። ደቡብ አፍሪካና ዚምባብዌ በነጭ አናሳዎችም ለዘመናት ተገዝተዋል፤ ተጨፍጭፈዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው ሃውልትም ይገርሰስ ጥያቄዎች በርክተዋል።